ሴቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጠቁት 10 የካንሰር ዓይነቶች

                                             

ካንሰር በአብዛኛው ከቤተሰብ የህክምና ታሪክ፣ ከምንከተለው የህይወት ዘይቤ እና ምርጫ እንዲሁም ከአካባቢው ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በእርግጥ በቤተሰባዊ የጤና ታሪክ ምክንያት የሚከሰትን ካንሰር ለመቆጣጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ በአካባቢ ሁኔታዎች ምክንያት የሚከሰተው ካንሰርም ቢሆን የመከላከል ዕድላችን አነስተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ አመጋገብ፣ ክብደት፣ የእንቅስቃሴ ሁኔታ፣ ሲጋራ ማጨስና በመሳሰሉት ከአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዙ ካንሰሮችን ለመከላከል ግን እንችላለን። ይህም ማለት ጤናማ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ ካንሰርን ለመከላከል ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ማለት ነው፡፡

‹‹ካንሰርን የመከላከል እርምጃዎች በአብዛኛው በራሳቸው በሰዎቹ እጅ የወደቀ ነው፡፡ ሰዎች ብርቱ ጥንቃቄን ካደረጉ ራሳቸውን ከካንሰርም ሆነ ከሌሎች ከማናቸውም በሽታዎች መከላከል ይችላሉ›› ያሉት በኒውዮርክ ሲቲ በሚገኘው የስሎአን ኬተርንግ መታሰቢያ የካንሰር ማዕከል ውስጥ በጃይኖኮሎጂ የህክምና ዘርፍ ስፔሻል ሐኪም የሆኑት ሪቻርድ ባራካት ናቸው፡፡

እስካሁን ባለው ሁኔታ ከሶስት ሴቶች መካከል ሁለቱ በካንሰር የመያዝ ዕድል አይገጥማቸውም፡፡ ይህም ሆኖ ካንሰር በዓለማችን ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሴቶችን ያጠቃል፣ ይገድላልም፡፡ በ2008 ብቻ በአሜሪካ ውስጥ ከ700,000 በላይ የሆኑ ሴቶች በካንሰር በሽታ ተጠቅተዋል። ሴቶችን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያጠቁት የካንሰር አይነቶች ደግሞ ከዚህ በታች የተጠቀሱት አምስቱ በዋነኝነት የሚጠቀሱና በገዳይነታቸውም የሚታወቁ ናቸው፡፡

1. የጡት ካንሰር (Breast cancer)

ይህ የካንሰር አይነት ከሴቶች የካንሰር ጉዳዮች 20 በመቶውን ሲሆን በየዓመቱ በካንሰር ምክንያት ከሚሞቱት ሴቶች መካከል 15 በመቶ የሚሆኑትን የሚገድለው ይኸው የካንሰር አይነት መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከ8 ሴቶች መካከል አንዷ በዚህ የካንሰር አይነት እንደምትጠቃም ተረጋግጧል፡፡

2. የሣንባ እና የመተንፈሻ አካላቶች ካንሰር (Lung and bronchus cancers)

በሴቶች ላይ ከሚከሰቱት የካንሰር አይነቶች ውስጥ 14 በመቶ የሚሆኑት የሚጠቁት በሣንባ እና በመተንፈሻ አካላቶች ካንሰር መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በየዓመቱ በካንሰር ከሚሞቱት ሴቶች መካከል 26 በመቶ የሚሆኑት ሟቾች ህመም ከዚሁ የካንሰር አይነት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከ16 ሴቶች መካከል አንዷ በዚሁ የካንሰር አይነት ትጠቃለች፡፡

3. የትልቁ አንጀትና የፊንጢጣ ካንሰር (Colon and rectal cancers)

በሴቶች ላይ ከሚከሰቱት የካንሰር ህመሞች ውስጥ 10 በመቶ የሚሆኑት ከትልቁ አንጀትና ከፊንጢጣ ካንሰር ጋር የተያያዙ ሲሆኑ ከካንሰር ሟቾች መካከል 9 በመቶ የሚሆኑትም በዚሁ የካንሰር አይነት የሚከሰት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ በየዓመቱ በካንሰር ከሚሞቱት ሴቶች መካከል 26 በመቶ የሚሆኑት ሟቾች ህመም ከዚሁ የካንሰር አይነት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ከ16 ሴቶች መካከል አንዷ በዚሁ የካንሰር አይነት ትጠቃለች፡፡

4. የማህፀን ካንሰር (Uterine cancer)

በሴቶች ላይ ከሚከሰቱት የካንሰር አይነቶች መካከል 6 ከመቶ የሚሆኑት የሚጠቁት በዚሁ የካንሰር አይነት ነው፡፡ በካንሰር ህመም ከሚሞቱት ሴቶች መካከል 6 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ ህመማቸው ከዚሁ የካንሰር አይነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከ41 ሴቶች መካከል አንዷ በዚሁ የማህፀን ካንሰር አይነት እንደምትጠቃም ተረጋግጧል፡፡

5. የነጭ የደም ሴል ካንሰር 

በካንሰር ህመሞ ከሚጠቁ ሴቶች መካከል 4 በመቶ የሚሆኑት ህመማቸው ከዚህ የካንሰር አይነት ጋር የተያያዘ ነው። በካንሰር ምክንያት ከሚሞቱት ሴቶች መካከል ደግሞ 3 ከመቶ የሚሆኑት የመሞታቸው ምክንያት ይኸው የነጭ የደም ሴል ካንሰር አይነት ሲሆን ከ53 ሴቶች መካከል አንዷ በዚሁ የካንሰር አይነት እንደምትጠቃም ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡

6. የጡት ካንሰር

የጡት ካንሰር ሴቶችን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያጠቁት የካንሰር አይነቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ሲሆን ለዚህ ካንሰር መከሰት በዋነኛነት የሚጠቀሱት ምክንያቶችም የሚከተሉት ናቸው፡፡

ዕድሜ፡- በጡት ካንሰር ከሚጠቁት ሶስት ሴቶች መካከል ሁለቱ ዕድሜያቸው ከ55 በላይ ነው፡፡

ቤተሰባዊ ታሪክ፡- አንዲት ሴት እናቷ፣ እህቷ ወይም ልጇ በጡት ካንሰር የተያዘች ከሆነ እሷም በዚህ ካሰር የመያዝ እድሏ እጥፍ ይሆናል፡፡

የቆዳ ቀለም፡- ጥቁር ቀለም ያላቸው ሴቶች በጡት ካንሰር አንዴ ከተያዙ የመሞት ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህም ሆኖ ካንሰሩ ብዙውን ጊዜ ከጥቋቁር ሴቶች ይልቅ የሚያጠቃው ነጭ ቀለም ያላቸውን ሴቶች ነው፡፡ ምክንያቱም የነጮቹ ዕጢ በፍጥነት የሚያድግ በመሆኑ ነው፡፡

የጡት ህብረ ህዋሳት፡-  የጡት ህብረ ህዋሳት አጀብ ብለው በብዛት የሚገኙ ከሆነ ሴቶች በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የጨረር ህክምና፡- ሴቶች ቀደም ሲል በደረታቸው አካባቢ የጨረር ህክምና አድርገው ከሆነ ዘግየት ብሎ በጡት ካንሰር ሊጠቁ ይችላሉ፡፡

– ከ12 ዓመት በፊት እና ከ55 ዓመት በኋላ የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች በዚህ የካንሰር አይነት የመጠቃት ዕድላቸው ከፍ ይላል፡፡

– የሚያረግዙ ወይንም ከ30 ዓመታቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያረግዙ ሴቶች በጡት ካንሰር ሊጠቁ እንደሚችሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

– የወሊድ መከላከያ እንክብሎችን መጠቀም ሌላው የጡት ካንሰርን የሚያስከትል ነገር ነው፡፡

– ለልጆቻቸው ጡትን የማያጠቡ

– ከመጠን በላይ የወፈሩ እና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች የሚያዘወትሩ

– በየቀኑ የአልኮል መጠጦችን በብዛት የሚጎነጩ (የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያመለክተው ለሰባት ዓመታት ያህል በሳምንት ሶስት ቀን አልኮል ሲጠጡ የነበሩ 1.3 ሚሊዮን ሴቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ለጡት ካንሰር ተጋልጠዋል)

– ፅንስ ካስወረዱ በኋላ በዚሁ ምክንያት የሚከሰተውን ሕመም ለማስወገድ ዳሶታይል ስቲበርስትሮል (DES) የተባለውን መድሃኒት የሚጠቀሙ።

– የወር አበባ መታየት ካቆመ በኋላ (ከ50 ዓመት በላይ) የሚደረግ የሆርሞን ህክምና፡፡

ለጡት ካንሰር መከሰት በዋነኛነት የሚጠቀሱት ምክንያቶች እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

7. የሣንባ እና የመተንፈሻ አካላት ካንሰር

እጅግ ገዳይ ናቸው ከሚባሉት የካንሰር አይነቶች መካከል በዋነናነት የሚጠቀሰው የሣንባ ካንሰር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን የካንሰር አይነት በቀላሉ መከላከል ይቻላል። የሣንባ ነቀርሳ ካለባቸው ሴቶች መካከል 80 ከመቶ የሚሆኑት እንዲሁም ከወንዶች ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆኑት ሲጋራ ማጨስን በማቆም ብቻ ራሳቸውን ከዚህ ካንሰር ነፃ ማድረግ ይችላሉ፡፡ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች በሣንባ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከማያጨሱት ከ10 እስከ 20 ጊዜ በላይ የሰፋ ነው፡፡ ሌሎቹ ለሣንባ እና ለመተንፈሻ አካላት ካንሰር የሚያጋልጡት ምክንያቶች ደግሞ፡-

– ከሚያጨሱ ሰዎች ጋር መዋልና ማደር

– ራይን ጋዝ

– ኃይለኛ መርዝ (Arsenic)

– ሬንጅ (Tar)

– ጥላሸት (Soot)

ጤናማ የሆኑ አመጋገብ፣ የአልኮል መጠጥ መቀነስና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በእቅድ ማከናወን በሣምባ እና በመተንፈሻ አካል ካንሰር የመያዝ አጋጣሚን ይቀንሳል፡፡

8. የትልቁ አንጀት እና የፊንጢጣ ካንሰር

በትልቁ አንጀት እና በፊንጢጣ ካንሰር ከሚጠቁት ሴቶች መካከል 90 ከመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ50 በላይ ነው። ለዚህ የካንሰር አይነት የሚያጋልጡት ምክንያቶች ደግሞ፡-

– የግለሰቡ ወይም የቤተሰብ ከአንጀት ካንሰር ጋር የተያያዘ ህክምና በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ትናንሽ ነፍሳት፣ የሰውነት እብጠትና የሆድ ዕቃ ህመም

– ልፍስፍስነት፣

– ሲጋራ ማጨስ

– የአልኮል መጠጦች ሱሰኝነት

– ከመጠን በላይ ሥጋ እና ስብነት የበዛባቸው ምግቦችን መመገብ እና አነስተኛ መጠን ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬዎችን መውሰድ ናቸው፡፡

ይህንን የካንሰር አይነት ለመከላከል ቁልፉ ዘዴ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ እና ፈጣን የመከላከል እርምጃ መውሰድ ናቸው። ትልቁ አንጀት እና ፊንጢጣ ከተጠቃ በኋላ የተጠቁት ሴሎች በአንጀት ውስጥ ለማደግ ከ10 እስከ 15 ዓመት ሊፈጅባቸው ይችላል፡፡ በመሆኑም በየጊዜው የአንጀትና የፊንጢጣ ምርመራ የምናደርግ ከሆነ ችግሩ ወደ ካንሰርነት ከመቀየሩ በፊት ልንከላከለው እንችላለን፡፡

በቅርቡ የአሜሪካው ብሔራዊ የጤና ኢንስቲቲዩት ባሰራጨው ዘገባ ደግሞ ካልሲየም እና የወተት ተዋፅኦ ምግቦች የአንጀትና የፊንጢጣ ካንሰርን ለመከላከል እንደሚያስችሉ ጠቁሟል። የጤና ኢንስቲቲዩት በ200,000 ወንዶችና በ200,000 ሴቶች ላይ ባካሄደው ለሰባት ዓመታት የዘለቀ ጥናት ካልሲየም የበዛባቸውን ምግቦች በየጊዜው መመገብ ይህንን የካንሰር አይነት ለመከላከል እንደሚያስችል አረጋግጧል፡፡

9. የማህፀን ካንሰር

ለማህፀን ካንሰር መከሰት በዋነኛነት የሚጠቀሰው ምክንያት የሆርሞን ለውጥ ነው፡፡ በተለይም ከአስትሮጂን ጋር የተያያዘ የሆርሞን ለውጥ ይህንን የካንሰር አይነት ሊያስከትል እንደሚችል ተረጋግጧል። በእንግሊዝኛ Uterine cancer ወይም Endometical ተብሎ ለሚጠራው የማህፀን ካንሰር በዋነኛነትና በመንስኤነት የሚጠቀሱት ምክንያቶች፡-

– ከተለመደው አማካይ በላቀ ሁኔታ የወር አበባ መደጋገም

– ለማርገዝ ያለመቻል

– የኤስትሮጂን ህክምና መውሰድ

– ከመጠን በላይ መወፈርና ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች በብዛት መመገብ

– ለጡት ካንሰር የሚወሰደውን ታሞክሲፈን የተባለውን መድሃኒት በፊትም ሆነ በአሁኑ ወቅት መውሰድ

– የትናንሽ ዕጢዎች በማህፀን ውስጥ መከሰት

– የዕድሜ መግፋት

– የስኳር ህመም

– ከአንጀት ካንሰር ጋር የተያያዘ ቤተሰባዊ የህመም ታሪክ

– ከጡት ወይም ከኦቫሪያን ካንሰር ጋር የተያያዙ ግላዊ ታሪክ

– የማህፀን ግድግዳ መወፈር ናቸው፡፡

10. የነጭ የደም ሴል ካንሰር

ይህ የካንሰር አይነት በነጭ የደም ሴል ውስጥ የሚከሰት ሲሆን የተፈጥሮ የመከላከል አቅምን በማውረድ በቆሽት፣ በጉሮሮ እና በአጥንት መቅኔ ውስጥ ካንሰር እንዲከሰት የሚያደርግ ነው፡፡ ለዚህ የካንሰር አይነት የሚያጋልጡት ምክንያቶች ደግሞ፡-

– የተዳከመ ተፈጥሯዊ የመከላከል አቅም

– ዕድሜ፡- በዚህ የካንሰር አይነት ከሚጠቁት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ነው፡፡

– ለፀረ ተክል እና ለፀረ ነፍሳት የሚሆኑ መድሃኒቶችን ለመሳሰሉት ኬሚካሎች መጋለጥ

– የተፈጥሮ የመከላከል አቅምን የሚያጠቁ ህመሞች

በነጭ የደም ሴል ካንሰርን ለማስወገድ ወይም ለመከላከል የሚያስችል ዘዴ እስካሁን ድረስ አልተገኘም፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ኤች.አይ.ቪ የመሳሰሉትን ተፈጥሯዊ የመከላከል አቅምን ከሚያሳጡ በሽታዎች ራስን መጠበቅ ከነጭ የደም ካንሰር ለመታደግ ያስችለናል፡፡ ምክንያቱም ይህንን የካንሰር አይነት ከሚያስከትሉት ህመሞች አንዱ ኤች.አይ.ቪ በመሆኑ ነው፡፡

ማጠቃለያ፡- የአኗኗር ዘይቤን በመቀየርና በማሻሻል፣ የአመጋገብ ለውጥን የመሳሰሉ ቀላል ለውጦችን በመፍጠርና በየጊዜው የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ከማንኛውም የካንሰር አይነት ራሳችንን ለመታደግ እንችላለን፡፡ ሴቶችን በማጥቃት ገዳይ ከሆኑት የካንሰር አይነቶች ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አምስቱን ገዳይ የካንሰር አይነቶች በዚህ መልኩ ካቀረብን ዘንድ ከማህፀን ካንሰር ጋር የሚያያዘውን የማህፀን አፍ ካንሰር በሚመለከት ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ማህጸን በእንግሊዝኛ (Uterus or womb) ተብሎ የሚጠራ እና በሴቶች ሆድ ውስጥ በፊኛ እና ፊንጢጣ መካከል የሚገኝ ደግሞም ሾጠጥ ያለ ቅርፅ ያለው ኦርጋን ነው፡፡ ይህ አካል ሴቶች በእርግዝና ወቅት ፅንሱ እስኪወለድበት ጊዜ ድረስ የሚያድግበት ነው፡፡

ማህፀን በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላል፡፡ እነሱም የማህፀን አፍ (Cervix or Mouth of uterus) እና ፅንሱን የሚይዘው አካል (corpus or body) የሚባሉት ናቸው፡፡ ኮርፐስ ማለትም ፅንሱን የሚታቀፈው አካል በማህፀን ገበር እና በጡንቻማ ህብረ ህዋሳት የሚዋቀር ነው። አብዛኛው የማህፀን ካንሰር የሚከሰተው ደግሞ በውስጣቸው ገበር ውስጥ መሆኑን ጥናቶች አረጋግጠውታል፡፡

በአሜሪካ በምትገኘው የኒውዮርክ ግዛት ውስጥ የማህፀን ካንሰር ሴቶችን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያጠቁት የካንሰር አይነቶች በ4ኛ ደረጃ የሚገኝ ነው፡፡ በየዓመቱ በዚህ ግዛት ውስጥ ከ3600 ሴቶች በላይ የሚሆኑት በዚህ የካንሰር አይነት እንደሚጠቁና 600 የሚሆኑት ደግሞ እንደሚሞቱ መዘገቡ የማህፀን ካንሰር ምን ያህል አደገኛ መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡

የማህፀን ካንሰር የሚያጠቃው የትኞቹን ሴቶች ነው?

አብዛኛዎቹ በማህፀን ካንሰር የሚጠቁት ሴቶች ዕድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ካንሰር ብዙውን ጊዜ የሚያጠቃው ዕድሜያቸው ከ45 እስከ 65 ባሉት ሴቶች ላይ ሲሆን ከጥቁር ሴቶች ይልቅ በነጭ ሴቶች ላይ እንደሚበረታም ተረጋግጧል፡፡

ለማህፀን ካንሰር መንስኤ የሚሆኑት ምንድናቸው?

በአሁኑ ወቅት ለማህፀን ካንሰር በዋነኛነት የሚጠቀሱት ምክንያቶች በግልፅ የሚታወቁ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ምክንያቶች ለአንዲት ሴት በዚህ አይነቱ ካንሰር መያዝ በምክንያትነት ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ሳይንቲስቶች ተስማምተውበታል፡፡

– የሆርሞን መዛባት፡- በአነስተኛ ዕድሜ የወር አበባን የሚያዩ፣ በጣም ዘግይተው የወር አበባ ማየትን የሚያቆሙ (የሚያርጡ)፣ አርግዘው የማያውቁ፣ የሙሉ ጊዜ እርግዝና ያላጋጠማቸው ወይም ጥቂት ልጆችን ብቻ የወለዱ ሴቶች በማህፀን ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

– የቤተሰብ ታሪክ፡- እናቶቻቸው፣ እህቶቻቸው ወይም ሴት ልጆቻቸው በማህፀን ካንሰር የተጠቁ ሴቶች እነሱም በዚህ በሽታ የመያዝ ዕድል ሊገጥማቸው እንደሚችል ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብ አባሎቻቸው በአንጀት ካንሰር የተጠቁ ሴቶች በማህፀን ካንሰር የመያዝ ዕድል ሊገጥማቸው እንደሚችል ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡

ከመጠን በላይ መወፈር፡- ከልክ በላይ የሚወፍሩ ሴቶች በማህፀን ካንሰር ሊያዙ ይችላሉ፡፡

የጨረር ህክምና፡- በሌላ የካንሰር አይነት ህመም ምክንያት በዳሌያቸው አካባቢ የጨረር ህክምና ያደረጉ ሴቶች በማህፀን ካንሰር የመያዝ ዕድል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡

ያልተመጣጠነ የሴታሴትነት ጾታዊ ሆርሞን፡- በህክምናው ቃል ፖሊሳይስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም (polycystic ovary syndrome (PROS)) የሚለው የሆርሞን መዛባት አይነት ሴቶች ያልተመጣጠነ የሴታሴትነት ጾታዊ ሆርሞን (imbalance of female sex hormones) በሚገጥማቸው ጊዜ የሚከሰት ሲሆን ይህም ሁኔታ የወር አበባ ዑደት መዛባትን፣ በዕንቁላል ማፍሪያቸው አካባቢ ውሃ የቋጠረ እብጠትን፣ ለማርገዝ ያለመቻልንና ሌሎችንም የጤና እክሎችን ያስከትላል፡፡ ከሁሉም በላይ ያልተመጣጠነ የሴታሴትነት ፆታዊ ሆርሞን ያለባቸው ሴቶች የማህፀን ካንሰር እንደሚገጥማቸው ተረጋግጧል፡፡

የሆርሞን ተጠቃሚነት፡- አንዳንድ ሴቶች በወር አበባ ጊዜያቸው መዛባት ምክንያት ሆርሞኖችን ለመተካት የሚያስችል የህክምና አይነትን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ የሆርሞን ህክምና ደግሞ የማህፀን ካንሰርን ሊያስከትል እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ይህም ሆኖ የወሊድ መከላከያ እንክብሎች በማህፀን ካንሰር የመያዝን አደጋ ይቀንሱታል፡፡

ታሞክሲፊን፡- የጡት ካንሰርን ለመከላከል የሚወሰድ የመድሃኒት አይነት ሲሆን ይህንን የመድሃኒት አይነት ለረዥም ጊዜ የሚጠቀሙ ሴቶች በማህፀን ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

ሌሎች ለማህፀን ካንሰር መከሰት የሚጠቀሱት ምክንያቶች

በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም የሚገኙት ታዋቂ ሳይንቲስቶች ለማህፀን ካንሰር መከሰት በዋነኝነት የሚጠቀሱ መንስኤዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥናት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ እስካሁን በተደረጉት ጥናቶች መሰረት ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ያልተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል መጠጣትና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ያለማድረግ ለማህፀን ካንሰር መከሰት በምክንያትነት የሚጠቀሱ ነጥቦች መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የስኳር ህመምተኛ የሆኑ ሴቶች እና በፓፒሎማ ቫይረስ የተጠቁ ሴቶች በማህፀን ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

የማህፀን አፍ ካንሰር 

የማህፀን አፍ በማህፀን ታችኛው ክፍል የሚገኝ ሲሆን ፈረንጆች ይህንን የማህፀን ክፍል አንዳንዴ ዩተረን ሴርቪክስ ብለው ይጠሩታል፡፡ ይህ የማህፀን ክፍል ማህፀንን ከብልት ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡ ለሰውነት አካል ቅርብ የሆነው የማህፀን አፍ ደግሞ ኢንዶሴርቪክስ ተብሎ ይጠራል። ከብልት ቀጥሎ የሚገኘው የማህፀን አፍ አካል ኤክሶ ሰርቪክስ ወይም ኤክቶሰርቪክስ ይባላል፡፡

የማህፀን አፍን ሸፍነው የሚገኙት ሁለቱ ሴል አይነቶች ሶክዋሞሴልስ እና ግላንዱላር ሴልስ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ እነኚህ ሁለት የሴል አይነቶች የሚገናኙበት ቦታ ደግሞ ትራንስፎርሜሽን ዞግ ተብሎ ይጠራል፡፡ አብዛኛው የማህፀን አፍ ካንሰር የሚከሰተውም በዚሁ ቦታ ላይ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ የማህፀን አፍ ካንሰር የሚጀምሩት በማህፀን አፍ ገበር ላይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሴሎቹ በድንገት ወደ ካንሰርነት የሚለወጡ አይደሉም፡፡ መደበኛ የሆኑት የካንሰር አይነቶች መጀመሪያ ቀስ በቀስ ወደ ቅድሞ ካንሰርነት መለወጥ ይጀምራሉ፡፡ የህክምና አዋቂዎች ይህንን የሴሎች የቅድመ ካንሰር ለውጥ በተለያየ ስም ይጠሩታል፡፡ ከእነኚህም መገለጫዎች መካከል ሰርቪካል ኢንትራኢፒቴሊያል፣ ስክዋሞስ ኢንትራኢፒቴሊያል ሌዝዩን እና ዳይስፕላዚያ ናቸው፡፡ ይሁንና እነኚህ የቅድመ ካንሰር ለውጦች በምርመራ ማወቅና በህክምና ካንሰር እንዳይዘን መከላከል እንችላለን፡፡

የማህፀን አፍ ካንሰር እና የቅድመ የማህፀን አፍ ካንሰሮች ምን አይነት ገፅታ እንዳላቸው በማይስክሮኮፕ እይታ መረዳት ይቻላል፡፡ የማህፀን አፍ ካንሰር በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች የሚከፈል ነው፡፡ እነኚህም ስኩዋሞስ ሴል ካርሲኖማ እና አዴኖካርሲኖማ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከማህፀን አፍ ካንሰሮች ውስጥ ከ80-90 በመቶ የሚሆኑት ስኩዋሞስ ሴል መሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል፡፡

ስኩዋሞስ ሴል ካርኪኖማ የተባለው የማህፀን አፍ ካንሰር አይነት ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው ኤክሶሰርቪክስ እና ኢንዶሰርቪክስ በሚገናኙበት ቦታ ላይ ነው።

ሌሎቹ የማህፀን አፍ ካንሰሮች ደግሞ ብዙውን ጊዜ አዴኖካርሲኖማ ተብለው የሚታወቁት ናቸው፡፡ የማህፀን አፍ አዴናካርሲኖማስ ላለፉት 20 እና 30 ዓመታት የተለመዱ ሆነዋል፡፡ ይህ የማህፀን አፍ ካንሰር የሚከሰተው ደግሞ ሙከስ ግላንድ ሴልን በሚያመርትበት በአዲኖካርሲሞናስ ውስጥ ነው፡፡

ምንም እንኳን የማህፀን አፍ ካንሰር ብዙውን ጊዜ በቅድመ ካንሰር የለውጥ ሂደት የሚከሰት ቢሆንም የቅድመ ካንሰር ለውጥ ከታየባቸው ሴቶች ውስጥ በካንሰሩ የሚጠቁት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ከቅድመ የማህፀን አፍ ካንሰር ወደ ዋናው የማህፀን አፍ ካንሰር ያለው ሂደት በርካታ ዓመታትን ይወስዳል፡፡ ይህም ሆኖ አንዳንዴ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዋናው ካንሰር ሊከሰትም ይችላል፡፡ በብዙዎች ሴቶች የቅድመ ካንሰር ሴሎች ያለ ምንም የህክምና ክትትል ሊወገዱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በአንዳንድ ሴቶች ግን ቅድመ ካንሰሩ ወደ እውነተኛውና ገዳዩ ካንሰርነት ሊቀየር ይችላል፡፡ በመሆኑም በቅድመ ካንሰር የለውጥ ጊዜ ውስጥ የሚደረግ ምርመራ እና የህክምና ክትትል ዋናው ካንሰር እንዳይከሰት ሊያደርግ ይችላል፡፡

የቅድመ ካንሰር ለውጦች በማህፀን ውስጥ እንደሚገኙት የሴል አይነቶች ሁኔታ የተለያዩ ናቸው፡፡ ይህንን የለውጥ ሂደት ማወቅ የሚቻለው ደግሞ በማይስክሮኮፕ አማካኝነት ሴሎችን በመመልከትና በመመርመር ነው፡፡

የማህፀን አፍ ካንሰርን መከላከል ይቻላል?

በአብዛኛው ዋና ዋናዎቹ የማህፀን አፍ ካንሰሮች በቅድመ ካንሰር ለውጥ የሚከሰቱ በመሆናቸው ይህ የካንሰር አይነት እንዳይስፋፋ ማድረግ የሚቻልባቸው ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ዘዴ የቅድመ ካንሰሩን ሂደት በማወቅ ወደ ዋና ካንሰርነት እንዳይቀየሩ መከላከል ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ደግሞ የቅድመ ካንሰር ለውጡ እንዳይከሰት በመከላከል ነው፡፡

የማህፀን አፍ ካንሰርን ለመከላከል ዋነኛው ዘዴ ካንሰሩ ወይም ቅድመ ካንሰሩ መኖሩን በምርመራ በማረጋገጥ እንዲወገድ በማድረግ ነው፡፡ በተለይም የቅድመ ካንሰሩ ለውጥ ወደ ዋናው ካንሰርነት እንዳይለወጥ መከላከል እጅግ ጠቀሜታነት አለው፡፡

ዋና ዋና ምክሮች

– እያንዳንዷ ሴት ዕድሜዋ 21 ዓመት ከሞላበት ጊዜ ጀምሮ የማህፀን አፍ ምርመራ ማድረግ ይኖርባታል፡፡ ዕድሜያቸው ከ21-29 የሆኑ ሴቶች ቢያንስ በየሦስት ዓመቱ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

– ከ30 ዓመታቸው ጀምሮ የHPV እና የPAP ምርመራዎችን በቅንጅት ቢያንስ በየአምስት ዓመቱ ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው፡፡

– ሌላው አማራጭ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 65 የሆኑት ሴቶች የPAP ምርመራን ብቻ በየሶስት ዓመቱ ማድረግ ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡

ምንጭ፦Mahdere Tena

Advertisement