12ቱ የኦቾሎኒ አስደናቂ የጤና በረከቶች Benefits of Peanuts

                                        

የስኳር በሽተኛ ከሆኑ ወይም ከፍተኛ የደም ግፊት የሚያስቸግርዎ ከሆነ ኦቾሎኒ ይጠቅምዎታል፡፡ በናያሲን (ቫይታሚን ቢ3) የበለፀገ ነው፡፡ ይህም ጎጂውን የኮሌስትሮል አይነት መቀነስ የጠቃሚውን መጠን ይጨምራል፡፡ ኦቾሎኒ በደም ቅዳዎች ላይ ዕጢዎችን እንዳይፈጠሩ የሚከላከለውን እና በአብዛኛው ከቀይ ወይን ጋር የሚያያዘውን resveratrol የተሰኘ ንጥረ ነገር ይዟል፡፡ በርካታ ጥናቶች በየዕለቱ አንድ ብርጭቆ ቀይ ወይን መጠጣት ለልብ ጥሩ እንደሆነ ቢገልፁም ኦቾሎኒ ግን ከወይን የበለጠ የresveratrol መጠን ይዟል፡፡

1. በማዕድናት የበለፀገ ነው
በፑርዱ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተደረገ ጥናት 28 ግራም (1 አውንስ) ኦቾሎኒ ወይም የኦቾሎኒ ቅቤ (Peanut butter) በየዕለቱ ከተመገብን የማግኒዚየም፣ ፋይበርን፣ ኮፐር፣ ቫይታሚን ኢ እና Arginine የተሰኙት ንጥረ ነገሮች መጠን ይጨምራል፡፡ እነዚህ ሁሉ የልብ በሽታን ለመከላከል ይጠቅማሉ፡፡ በዚህ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው ጥናት የኦቾሎኒ ሌላ ጠቀሜታንም አሳይቷል፡፡ ኦቾሎኒ ረሃብን በማስታገስም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ በቅርብ ያገኙት ምግብ ኦቾሎኒን ብቻ ከሆነ ይመገቡት፡፡ ረሃብዎን ለሁለት ሰዓት ተኩል ያህል ያስታግስልዎታል፡፡ ከ20-30 ደቂቃ በላይ ከማይዘልቁት ኬኮች እና ሌሎች ስናኮች ጋር ስናነፃፅረው ኦቾሎኒን የሚደርስበት የለም፡፡

2. ኦቾሎኒ እና ካንሰር
በፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት ኦቾሎኒ በበሽታ ተከላካዮች የበለፀገ ነው ብሏል፡፡ ይህም ለልብ እና ለካንሰር በሽታዎች የሚያጋልጡንን ፍሪ ራዲካልስ ለመከላከል ያስችለናል፡፡ ከእነዚህ በሽታ ተከላካዮች ውስጥ P-coumaric acid የተሰኘው ኦቾሎኒው ሲቆላ የመከላከል ብቃቱ በ22% ይጨምራል፡፡

3. ስኳር በሽታን በኦቾሎኒ
ኦቾሎኒ የኮሌስትሮልን መጠንን ዝቅ በማድረጉ ረገድ የተመሰከረለት ከመሆኑም በላይ type 2 በተሰነው የስኳር ህመም ለተጠቁ ሰዎችም ይጠቅማል፡፡ ምግብ ከተመገቡ በኋላ የኢንሱሊን መጠን መጨመር የሚያጋጥም ሲሆን ኦቾሎኒ ይህን ችግር ያረጋጋል፡፡

4. መውለድን ያበረታታል
ኦቾሎኒ የሴቶችን ጤናማ ልጅ የመውለድ ዕድልን የሚጨምረውን folate የተባለ ንጥረ ነገር በጥሩ መጠን ይዟል፡፡ በዘርፉ በተደረጋጋሚ የተካሄዱ ጥናቶች በየእለቱ 400 ማይክሮግራም የፎሊክ አሲድ እንክብል በእርግዝና ወራት የሚወስዱ እናቶች በልጆቻቸው ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጤና እክሎችን በ70% ለመቀነስ ያስችላል፡፡

5. የደም የስኳር መጠንን ያረጋጋል
ከሩብ ኩባያ ኦቾሎኒ ሰውነታችን ከሚያስፈልገው ማንጋኒዝ 35% ያህሉን እናገኛለን፡፡ ይህ ሚኒራል ስብ እና ካርቦሃይድሬትን ይቀንሳል፡፡ ሰውነታችን ካርቦሃይድሬትስን እንዲያዋህድ ይረዳል፤ የደም የስኳር መጠንን ያስተካክላል፡፡

6. የሐሞት ጠጠርን ይከላከላል
ኦቾሎኒ የሀሞት ጠጠር እንዳይፈጠር ይከላከላል መባሉ ሊያስገርም ቢችልም የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት የተካሄዱ ጥናቶች በሳምንት 28 ግራም (የ1.00 ብር ኦቾሎኒ) የሚመገቡ ሰዎች የሐሞት ጠጠር በሰውነታቸው ውስጥ የመፈጠር ዕድሉ በ25% ይቀንሳል ተብሏል፡፡

7. ድብርትን ይዋጋል
ኦቾሎኒ Typtophan የተባለው አሚኖ አሲድ ጥሩ መገኛ ነው፡፡ ይህ አሚኖ አሲድ ሴሮቶኒን የተባለው ቁልፍ የአንጎል ኬሚካል እንዳይዋዥቅ ያደርጋል፡፡ ድብርት ሲያጋጥም ወደ አንጎል ሴሎች የሚለቀቀው የሴሮቶኒን መጠን ይቀንሳል፡፡ Tryptophan የሴሮቶኒንን የፀረ ድብርት ተፅዕኖ እንዲጨምር የሚያደርገው በደም ውስጥ የሴሮቶኒን መጠን በማሳደግ ነው፡፡

8. የማስታወስ አቅምን ይጨምራል
ኦቾሎኒ አለነገር ‹‹የአዕምሮ ምግብ›› የሚለው ስም አልተሰጠውም፡፡ በውስጡ የያዘው ቫይታሚን ቢ 3 ወይም ናያሲን አዕምሯችን የተለመደ ተግባሩን በብቃት እንዲወጣና የማስታወስ አቅማችን እንዲጨምር የማድረግ ብቃት አለው፡፡

9. በልብ በሽታ የመጠቃት ዕድልን ይቀንሳል
በርካታ ጥናቶች ኦቾሎኒን በቋሚነት መመገብ በልብ በሽ የመጠቃት ዕድልን እንደሚቀንስ ገልፀዋል፡፡ ኦቾሎኒ ለልብ ተስማሚ በሆኑ ሚኖአንሳቹሬትድ ፋትስ እና በሽ ተከላካዮች የበለፀገ ነው፡፡ በሳምንት ቢያንስ አራት ቀን ያህል ኦቾሎኒ ይመገቡ፤ በልብ የደም ስር በሽታዎች እና በሌሎችም የልብ ህመሞች የመጠቃት አጋጣሚዎችን በእጅጉ ይቀንሳሉ፡፡

10. ከእርጅና ጋር ተያይዞ የሚመጣ የመርሳት ህመምን ይከላከላል
ኦቾሎኒ አልዛይመርን የመሳሰሉ የመርሳት ህመሞችን በመከላከል ረገድ ያለውን ውጤት ለማወቅ በተደረገ ጥናት ላይ ከተሳተፉ ሰዎች ውስጥ ኦቾሎኒን በቋሚነት የሚወስዱት የመጠቃት ዕድላቸው በ70% ቀንሶ ተገኝቷል፡፡ የጥናቱ ውጤትም በየዕለቱ ሩብ ኩባያ ኦቾሎኒ መመገብ በቂ ናያሲን ለማግኘት ይረዳል ብሏል፡፡

11. ክብደት መጨመርን ይከላከላል
በቋሚነት ኦቾሎኒን መመገብ ክብደት እንዳይጨምር አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የተካሄደ ጥናት ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ ኦቾሎኒ የሚመገቡ ሰዎች ምንም ከማይበሉት ጋር ሲነፃፀር ክብደት የመጨመር ዕድላቸው ቀንሶ ተገኝቷል፡፡

12.የጨው መጠኑ ዝቅተኛ ነው
ከፍተኛ የጨው (ሶዲየም) መጠን የደም ግፊት እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ኦቾሎኒ ዝቅተኛ የጨው መጠን አለው፡፡ ይህም ጤናማ ልብ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡

ጥብቅ ማሳሰቢያ
ኦቾሎኒ ምንም አይነት አስገራሚ ፈውስና የጤና ጠቀሜታ ቢኖረውም እርስዎ ግን አለርጂክ ከሆኑ አንዲትም ፍሬ መብላት አይኖርብዎትም፡፡ በአብዛኛው በኦቾሎኒ የሚነሳ አለርጂ እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ኦቾሎኒን አዘውትረው ለመመገብ ከመወሰንዎ በፊት ሐኪምዎን ያማክሩ፡፡

ምንጭ:  የጤና ሞግዚት

Advertisement