ከ6 ሰዓት ያነሰ የእንቅልፍ ጊዜ ያላቸው ሰዎች ለልብ ህምም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው

ከስድስት ሰዓት ያነሰ የእንቅልፍ ጊዜ ያላቸው ሰዎች ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ፡

በየዕለቱ ከስድስት ሰዓት ያነስ እንቅልፍ የማያገኙ ሰዎች አርተሪ የተባሉ የደም ስሮቻቸው ላይ እንከን አንደሚፈጠር እና ለልብ ጤና ችግር ያላቸው ተጋላጭነት እንደሚጨምር ተገልጿል፡፡

በጥናቱ እድሜያቸው በአማካይ 46 ዓመትና ከልብ በሽታ ነፃ የሆኑ 4 ሺህ ስፔናዊያን  ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡

ጥናቱ ከስድስት ሰዓት ያነሰ እንቅልፍ የሚያገኙ ተሳታፊዎች በአማካይ ከ7 እስከ 8 ሰዓት እንቅልፍ ከሚያገኙ ተሳታፊዎች ጋር ሲነፃፀሩ÷ 27 በመቶ አርተሪ የተባለው ደም ስራቸው የመጥበብና በተገቢው መንገድ ደም ያለማዘዋወር ችግር መጋለጣቸውን አሳይቷል፡፡

ይህ ጥናት አርተሪ በተባለው የደም ስር መጥበብና በእንቅልፍ እጥረት መካከል ያለው ተዛምዶ ላይ ትኩረት አላደረገም ተብሏል፡፡

በየቀኑ በአማካይ የ8 ሰዓት ያህል እንቅልፍ ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን÷ ከሚፈለገው በላይ እንቅልፍ መተኛትም ለልብ ጤና ችግር  የራሱ የሆነ ተጽኅኖ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

የእንቅልፍ ችግር ያለባቸው ሰዎች የካፊን ንጥረ ነገር ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑ መጠጦችና አልኮል የመውስድ ልምምድ እንዳላቸው ተነግሯል፡፡

አንዳንድ ሰዎች አልኮል መውሰድ እንቅልፍ ለመተኛት እንደሚያስችል እምነት ያላቸው ሲሆን÷ አልኮል ወዲያውኑ አንቅልፍ እንዲወስድ ቢያደርግም አንዴ ከነቁ በኋላ ተመልሰው ለመተኛት አስቸጋሪ በመሆኑ እንቅልፍን የሚያዛባ መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡

የልብ በሽታ ተጋላጭነት ለመቀነስ ከሚያስችሉ አማራጮች መካከል መድሃኒቶች፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የአመጋገብ ስርዓትን ማስተካከል እንደሚገባ የጥናቱ መሪ ጆዜ ኦርዶቫስ ይናገራሉ፡፡

በአጠቃላይ በቂና ተመጣጣኝ እንቅልፍ የልብ በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንደሚያስችል በጥናቱ እንደተረጋገጠ ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.