የሜቴክ የህዳሴ ግድብ ውል ለፈረንሳይና ጀርመን ኩባንያዎች ሊሰጥ ነው

ትናንት ረፋድ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዶ ነበረ።

በውይይቱ ላይ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ክንውኖች ላይ ማስተካከያ በማድረግ ፕሮጀክቱ ከአራት ዓመታት በኋላ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

ፕሮጅክቱ ሲጀመር የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል የተባለበትን ቀነ ገደብ ካለፈ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ትናንት በተካሄደው ውይይት የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከግንባታው በፊት ጥልቅ ምርምርና ጥናት ባለመደረጉ ግንባታው ሊዘገይ እንደቻለ የገለፀ ሲሆን የግድቡ ግንባታ መዘግየት ሃገሪቱ በየዓመቱ 800 ሚሊየን ዶላር እንድታጣ አድርጓታል ተብሏል።

በአጠቃላይ ግድቡ አሁን የሚገኝበት ደረጃም 65በመቶ መሆኑ ተነግሯል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን የኢንጅነር ስመኘው በቀለን ህልፈት ተከትሎ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ያለበትን ደረጃ፣ የግድቡ ግንባታ የተስጓተተበትን ምክንያት እንዲሁም ወደ ፊት በግንባታው ላይ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮ ከቢቢሲ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ለግድቡ መጓተት በዋነኝነት የሚቀመጠው ምክንያት ምንድን ነው?

ዋና ሥራ አስኪያጁ ለግንባታው ስራ መጓተት ዋነኛው ምክንያቶች የኤሌክትሮ መካኒካል እና የብረታ ብረት ስራዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መጓዝ ስላልቻሉ ነው ይላሉ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የእነዚህ ስራዎችን ውል ሰጥቶ የነበረው ለመከላከያ ብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ፤ ሜቴክ መሆኑን ያስታወሱት ኢንጂነሩ፤ ፕሮጄክቱ መዘግየቱን ተከትሎ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ዙሪያ የህዝቡ አመኔታ እየቀነሰ በመምጣቱ መንግሥት ከሜቴክ ጋር የነበረውን ውል ከአንድ ወር ገደማ በፊት ሙሉ በሙሉ በማቋረጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ ተቋራጮች ጋር ውል ለመግባት ድርድር ላይ እንዳለና ሥራ የጀመሩ ተቋራጭችም እንዳሉ ገልፀዋል።

”ከዚህ በፊት በተቆራረጡ ውሎች ነበር ስራዎች ሲከናወኑ የነበሩት። አንዱ የአንዱን ሥራ ካዘገየ ኃላፊነት የሚወስድ አልነበረም። ስለዚህ ሥራውን በወጥነት ለማከናወን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሥራ ልምድ ካላቸው የጀርመን እና ፈረንሳይ ሃገራት ኩባንያዎች ጋር ድርድር እያደረግን ነው። የተወሰኑትም ወደ ሥራ ገብተዋል” ይላሉ።

ለተርባይን እና ጄኔሬተር ጂኢ አልስቶም ከተሰኘ የፈረንሳይ ኩባንያ ጋር እንዲሁም ለተርባይን-ጄኔሬተር አቅርቦት እና ተከላ ከጀርመኑ ቮኢዝ ኩባንያ ጋር ውል ለማሰር እየተነጋገሩ እንደሆነም ገልፀውልናል።

ፈርሶ እንደ አዲስ የሚሰራ ወይም ማስተካከያ የሚደረግበት የግድቡ አካል አለ?

ኢንጂነር ክፍሌ ፈርሶ እንደ አዲስ የሚገነባ የግድቡ አካል የለም ይበሉ እንጂ ውል የሚገቡት የውጪ ኩባንያ የተሰሩት ስራዎች ደረጃቸውን ስለመጠበቃቸውና ትክክል ስለመሆናቸው በቂ ፍተሻ ያደርጋሉ ይላሉ።

”የብረታ ብረት ስራ ውልን ሙሉ ለሙሉ ለውጪ ኩባንያ እንሰጣለን። የውጪ ኩባንያ ይህን ውል ሲቀበል ከዚያ በፊት የተሰሩ ስራዎች ጥራት እንዳላቸው የማረጋገጥ ኃላፊነትን ጭምር ነው አብሮ የሚወስደው” ብለዋል።

ቀደም ሲል በሜቴክ ፋብሪካዎች የተሰሩ የውሃ መዝጊያ እና የውሃ ማስተላለፊያ አሸንዳዎች አሉ። በግድቡ ላይ የተተከሉም አሉ። እነዚህ በትክክል ተተክለዋል ወይ? በትክክል ተበይደዋል ወይ? ብሎ የማጣራት ግዴታ አለባቸው። የጎደለ ወይም ስህተት ያለበት ካለ ፈትሾ የማስተካከል እንጂ ፈርሶ እንደ አዲስ የሚገነባ ነገር የለም።” ይላሉ ኢንጂነር ክፍሌ።

ህዳሴ ግድብ ከአራት ዓመታት በኋላስ እንዴት ይጠናቀቃል?

ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደሚሉት ከሆነ የህዳሴው ግድብ ከጅምሩ ዋነኛ ችግሩ ”ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የጊዜ ሰሌዳ አልነበረውም።”

ይህ ይሁን እንጂ እሳቸው ”ተጨባጭ ነው” በሚሉት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግድቡ ከአራት ዓመታት በኋላ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት እንደሚችል ባለ ሙሉ ተስፋ ናቸው።

”ይህ ፕሮጀክት የበጀት ችግር ገጥሞት አያውቅም። ወደፊትም አይገጥመውም። መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚያከናውነው ፕሮጀክት ነው።” የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ ለግድቡ መጠናቀቅ ወሳኝ የሚባሉ ስራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው መሰራት በመጀመራቸው ግድቡ በፍጥነት እና በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይጠናቀቃል።

በግድቡ ግንባታ ላይ ወደፊት ሊኖሩ የሚችሉ ፈተናዎችስ?

‘”ህዳሴ ግድብ በጣም ውስብስብ የሆነ ፕሮጀክት ነው።” የሚሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ ግድቡ ሲከናወን ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶች ምንድናቸው? እነዚህን ችግሮች እንዴት ነው ማለፍ የሚቻለው? የሚሉትን ጥያቄዎች እና ምላሾች ቀድሞ ማወቅ የፕሮጅክቱ ሥራ አስኪያጅ ኃላፊነቶች መካከል ዋነኛው ነው።

ግድቡ ውሃ እንዲይዝ ማድረግ በራሱ አንዱ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

“በግድቡ ግንባታ ላይ እክል ሊሆኑ የሚችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ቀድሞ ለመለየት እንጥራለን፤ ለችግሮቹም መፍትሄ እየሰጠን እንሄዳለን” ይላሉ ኢንጂነር ክፍሌ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.