በሚፈጸምባቸው የተለያዩ ጥቃቶች ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉ ታዳጊዎች ቁጥር ጨምሯል

 

በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ  በሚፈፀሙ የተለያዩ ጥቃቶች ምክንያት ራሳቸውን የሚያጠፉ ታዳጊዎች መበራከታቸው ተገለፀ።
በአፍላ ዕድሜ ክልል ወስጥ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የሚደርሱ ማግለልና መድሎዎች፣ በቤተሰብ የሚደርሱ አካላዊ ጥቃቶች፣ ጾታዊ ትንኮሳዎችና  እና መሰል ድርጊቶች ታዳጊዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ የሚያደርጉ ምክንያቶች መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል።
ይህም የወጣቶቹን በራስ መተማመን በመሸርሸር ለአእምሮ ጭንቀት እና ተጓዳኝ በሽታዎች የሚዳርግ መሆኑን በለንደን የሚገኘው  ኪንግስ ኮሌጅ ባካሄድው ጥናት ይፋ አድርጓል።
ይህ ሁኔታ በጉልምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙ ወጣቶች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ግን  አነስተኛ መሆኑ ነው የተገፀው።
ባለፈው ዓመት አለም የጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሰረት እራስን በማጥፋትና እራሳቸውን ላይ ጉዳት በማድረስ የሚሞቱ ወጣቶች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ያመላክታል።
በሪፖርቱ መሰረትም በፈረንጆቹ 2017 በዓለም እራስን ለከፍተኛ ጉዳት በመዳረግና እራስን በማጥፋት ለህልፈት የተዳረጉ ታዳጊዎች ቁጥር 67 ሺህ መድረሱ ነው የተገለፀው።
ይህ አሃዝም በፈረንጆቹ 2015 ላይ በድንገተኛ አደጋ፣ በመተንፈሻ አካላት መታወክ እና በእርግዝና ወቅት በሚፈጠር ችግር ምክንያት ለሞት ከተዳረጉ ወጣቶች ቁጥር ጋር የሚቀራረብ መሆኑ ተገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በተለይም በትምህርት ቤቶችና በማህበራዊ ህይወት አካባቢ በአፍላ ዕድሜ ላይ በሚገኙ ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በርካታ ታዳጊዎችን ለሞት እየዳረገ መሆኑን የኪንግስ ኮሌጁ ተመራማሪ ጄሴ ባልድዊን ተናግረዋል።
በመሆኑም በተጠቀሰው ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን ከማግለል ይልቅ በሚደርሱባቸው ችግሮች ዙሪያ በመወያየት እና የሥነ ልቦና ችግር እንዳይደርስባቸው ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በአፍላ ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ቅርበት ያለው ማንኛውም ሰው የታዳጊዎችን ስሜት በደንብ በመረዳትና በማማከር ራሳቸውን ከማጥፋት አደጋ መታደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.