አይ ኤም ኤፍ ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት አበረታች ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገቧን ገለጸ

አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ኢትዮጵያ ባለፉት አስር አመታት አበረታች ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገቧን ገለጸ።

አይ ኤም ኤፍ የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፥ በሃገሪቱ የተመዘገበው እድገት ድህነትን በመቀነስ የበርካታ ዜጎችን ህይዎት መቀየር መቻሉንም አመላክቷል።

ከዚህ ባለፈም በሃገሪቱ የተከናወኑ የመሰረት ልማት ዝርጋታዎች ትምህርትና ጤና የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ምቹ አጋጣሚ መፍጠራቸውንም አንስቷል።

አሁን ላይም ሃገሪቱ በተደረጉ ማሻሻያዎችና በግሉ ዘርፍ በታዩ ለውጦች ወደ ተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት እያመራች መሆኗን አንስቷል።

ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት በፈረንጆቹ 2017/18 አነስ ባለ መጠን የ7 ነጥብ 7 በመቶ እድገት ያስመዘገበው ሀገራዊ እድገት፥ ፖለቲካዊ ሁኔታ ሲሻሻልና መቀዛቀዝ ያሳየው ኢንቨስትመንት ሲያገግም 8 ነጥብ 5 በመቶ ይሆናልም ብሏል።

በተደረጉ ማሻሻያዎችም የበጀት ጉድለት ክፍተቱ እየተስተካከለ መሆኑን ጠቅሶ፥ ከፍ ብሎ የነበረው ሃገራዊ የዋጋ ግሽበትም ወደ አንድ አሃዝ ይወርዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል።

ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ለማስቀጠል የመንግስት ወጪን መቀነስ፣ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ላይ ለግሉ ዘርፍ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን ማስወገድ፣ ከውጭ ብድር ይልቅ ገቢን በሃገር ውስጥ ምንጭ ማዳበር እንደሚገባም ተቋሙ ምክረ ሃሳቡን ሰንዝሯል።

ይህም የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠርና የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እንደሚረዳ በመጥቀስ።

የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሻሻልና በኢኮኖሚው ተወዳዳሪነትን ማስፈንም መንግስት በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥቷል።

በሃገሪቱ ከታየው እድገት ባሻገር ግን ከፍተኛ የሆነው የብድር እዳ ጫና ለኢኮኖሚያዊ እድገቱ ትልቁ ፈተና ሆኖ ይቀጥላልም ነው ያለው ሪፖርቱ።

የተቋሙ ባለሙያዎችም መንግስት አሁን ያለበትን ከፍተኛ የብድር እዳ ጫና ለመቋቋም የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦችን አስቀምጠዋል።

በዚህም በረጅም ጊዜ እና በአነስተኛ ወለድ የሚከፈሉ የብድር አማራጮችን መጠቀም እና አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ከግብር የሚገኘውን ገቢ ማሻሻልና ማጠናከር እንዲሁም የወጪ ገቢ ንግድን ማስፋፋትም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራባቸው ይገባል ብለዋል።

ሪፖርቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስተዳደር ኢኮኖሚውን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ለማድረግና ሃገራዊ እድገቱን ለማስቀጠል አበረታች ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ማድረጉንም አስታውሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህም ተግባራዊ ያደረጉት አካታችና ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይትም በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ማምጣቱንም አውስቷል።

ከዚህ ባለፈም የእርሳቸው አስተዳደር የጾታ እኩልነትን ለማምጣት የወሰዳቸው እርምጃዎች ሃገሪቱን በኢኮኖሚ እድገቱ ተጠቃሚ ያደርጓታልም ብሏል ሪፖርቱ።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.