የአየር ንብረት ለውጥ፤ የት ደረስን?

ወደ 200 የሚጠጉ የሃገራት ተወካዮች በአውሮፓዊቷ ሃገር ፖላንድ ተሰባስበው ስለ የአየር ንብረት ለውጥ ይመክራሉ፤ ይህም የፓሪሱን ስምምነት ትግበራ ያጠናክራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

የተባበሩት መንግሥታት 2015 ላይ በፓሪስ የተደረሰውን ስምምነት እንደ አሜሪካ እና አውሮፓ ያሉ ግዙፍ ኢኮኖሚዎች በገቡት ቃል መሰረት ስምምነቱን እየተገበሩት ስላልሆነ የዓለም ሙቀት መጨመር አሳስቦኛል ብሏል።

የዓለምን ሙቀት መጨመረ የሚከታተሉት ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ምንም እንኳ የፓሪሱ ስምምነት የዓለምን ሙቀት ከ2 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ እንዳይጨምር ለማደረግ ቃል የተገባ ቢሆንም፤ መሆን የነበረበት ግን ከ1.5 ዲግሪ ሴሊሺየስ በታች ነበር።

የዓለም ሙቀት ምን ያክል እየጨመረ ነው? ምንስ ማድረግ ይቻለናል?

ዓለማችን ከመቼውም በላይ እየሞቀች ነው። እንደ የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት ከሆነ፤ በዓለም ዙሪያ ኢንዱስትሪው ከመስፋፋቱ በፊት ከነበረው የአየር ጠባይ ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ሰዓት የዓለማችን ሙቀት በአንድ ዲግሪ ጨምሯል።

በዚህ አካሄድ 2100 ላይ የዓለም ሙቀት ከ3-5 ዲግሪ ሰሊሺየስ የሚጨምር ይሆናል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ ዲግሪ ሴሊሺየስ ሲባል ከፍተኛ ለውጥ ላይመስል ይችላል። ይሁን እንጂ የዓለም መንግሥታት የዓለም ሙቀትን ለመቀነስ አስቸኳይ እርምጃ ካልወሰዱ፤ የባህር ወለል ይጨምራል፣ የባህር ሙቀት እና አሲዳማነት የከፋ ይሆናል እንዲሁም ሩዝ፣ በቆሎ እና ስንዴ የማብቀል አቅማችን አደጋ ላይ ይወድቃል።

ይህ ዓመት በመላው ዓለም ከተለመደው በላይ ረዥም የሙቀት ወቅት እና ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ዓመት ነው።

ሰሜናዊ ንፍቀ-ክበብ ማለትም አውሮፓ፣ እስያ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ሰሜን አፍሪካ ከፍተኛ ሙቀት ተስተውሎባቸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የታለመው ዕቅድ የሚሳካ አይመስልም

በተገባው ቃል መሰረት የፓሪሱ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ቢደረግ እንኳ በዚህ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ምድራችን ከ3 ዲግሪ ሴሊሸየስ በላይ ሙቀት ትጨምራለች።

የዘርፉ ባለሙያዎች ለበርካታ ዓመታት የዓለም ሙቀት ከ2 ዲግሪ ሴሊሺየስ በታች ሆኖ መቆየት አለበት በማለት ሲወተውቱ ቆይተዋል።

አሁን ላይ ግን የዓለም ሙቀት ከ1.5 ዲግሪ ሴሊሺየስ በታች መሆን አለበት ይላሉ።

ቻይና እና አሜሪካ ከፍተኛ አመንጪዎች ናቸው

በዓለማችን በካይ አየር በመልቀቅ ቻይና እና አሜሪካ ላይ የሚደርስባቸው የለም። በጠቅላላው ከሚለቀቀው በካይ አየር 40 በመቶው የሚሆነው ከቻይና እና አሜሪካ የሚወጣ ነው። ህንድ፣ ሩሲያ፣ ጃፓን፣ ብራዚል፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኢራን፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በካይ አየር ከሚለቁ የመጀመሪያዎቹ 10 በካይ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ይገኙበታል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከፓሪሱ ስምምነት እራሳቸውን እንደሚያገሉ ዝተው ነበር። በወቅቱ ትራምፕ የአሜሪካንን ንግድ እና ሰራተኞች የማይጎዳ ”የተሻለ” ስምምነት እንዲኖር እሰራለሁ ብለው ነበር።

ከተሞች በተለየ መልኩ አደጋ ውስጥ ናቸው

ቬሪስክ ማፕልክሮፍት የተባለ ድርጅት ጥናት ይፋ እንዳደረገው፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከፍተኛ አደጋ የተጋረጠባቸው 95 በመቶ የሚሆኑት ከተሞች በአፍሪካ ወይም በእስያ የሚገኙ ናቸው። የ20 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያዋ የናይጄሪያዋ ሌጎስ እና የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ መዲና ኪንሻሳ የመሳሰሉ በፍጥነት እያደጉ የሚገኙ ከተሞች ይገኙበታል።

የአክቲክ የበረዶ ግግር አደጋ ላይ ነው

በቅርብ ዓመታት የአርክቲክ የበረዶ ግግር መጠን በፍጥነት እየቀነሰ ነው። 2012 ላይ ዝቀተኛው ደረጃ አስመዝግቦ ነበር።

የሚለቀቀው በካይ አየር ካልቀነሰ የአርክቲክ ውቅያኖስ 2050 ላይ በረዶ አልባ ሊሆን ይችላል።

እኛ ምን ማድረግ እንችላለን?

ትልቁ ኃላፊነት እና ለውጥ ማስመዝገብ የሚችሉት መንግሥታት ቢሆኑም፤ ግለሰቦችም የራሳቸውን ኃላፊነት መወጣት ይችላሉ።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት አንድ ግለሰብ የአኗኗር ዘዬውን በመቀየር እየደረሰ ያለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል፤ ለዚህም የሚከተለውን ያስቀምጣሉ።

ስጋ፣ ወተት፣ አይብ እና ቅቤ በትንሹ እንጠቀም። በአካባቢያችን የሚመረቱ ወቅታዊ የሆኑት አትክልት እና ፍራፍሬዎችን አዝወትረን እንመገብ። በተቻለ መጠን የምግብ ብክነትን እንቀንስ። በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ መኪኖችን እናሽከርክር አጭር እርቀቶችን ደግሞ በእግራችን እንጓዝ አሊያም ሳይክል እንጋልብ። ከአወሮፕላን ይልቅ የባቡር እና አውቶብስ አማራጮችን እንጠቀም። ለስብሰባ ረዥም ጉዞዎችን ከማድረግ ይልቅ በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንገናኝ። አነስተኛ የካርበን ልቀት ያላቸውን የቤት ውስጥ መገልገያዎችን እንምረጥ።

ሳይቲስቶቹ ጨምረው እንደሚሉት ከሆነ ሰዎች አነስተኛ ስጋ እና የስጋ ውጤቶችን ቢመገቡ በከፍተኛ ደረጃ የአየር ብክለትን መቀነስ ይቻላል። አስተኛ ስጋ እና የስጋ ውጤቶችን በመጠቀም የስጋ ማቀነባበሪያ ኢንደስቱሪዎች የሚለቁትን የካርበን ልቀት መጠንን መቀነስ ይቻላል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.