የዓይን ጤናን ለመጠበቅ የሚረዱ አብይ ተግባራት

Natural Beauty Portrait

የዓይን ጤና ችግሮች ሲከሰቱ ወቅታዊና ተገቢ ህክምና ከማድረግ በተጨማሪ ችግሮች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ ማድረግና የዓይንን አጠቃላይ ጤና መጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራትን ማከናወን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የዓይን ጤናን ለመጠበቅ የሚረዱ የእንክብካቤ እና የጥንቃቄ ድርጊቶችን በአጭሩ፡-
ዋና ዋናዎቹ
• ጤናማ የአመጋገብ ስርአት መከተል
• ለጤና ጠንቅ ከሆኑ ልምዶች እራስ መጠበቅ
• ዓይንን ከአደጋ መጠበቅ
• የቴክኖሎጂ ምርቶችን አጠቃቀም ማስተካከል
• መደበኛ የአካለ ብቃት እንቅስቃሴ እና
• መደበኛ የዓይን ምርመራ ማድረግ ናቸው፡፡

1) ጤናማ የአመጋገብ ስርአትን መከተል
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ለአጠቃላይ ጤና ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ለዓይን ጤና ከፍተኛ አስተዋጾ አለው፡፡ በተለይም በቪታሚንና በማዕድናት የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ የዐይን ልባስ ፣የሌንስና የሬቲናን ጤናና ስራ የተሳለጠ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡
ቪታሚንና ማዕድናት በተለይም ቫይታሚን ‹‹ኢ››፣ ቫይታሚን ‹‹ሲ›› እና ዚንከ በዓይን ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ በደም ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎችን ሀይል ለማዳከም ከእድሜ መግፋት ጋር ትያይዘው የሚመጡ በተለይም የሰገነተ ዕይታ መጃጀትና የዐይን ሞራ በቶሎ እንዳይከሰቱ ለማድርግና የጉዳቱንም መጠን ለመቀነስ ይረዳሉ፡፡
በቫየታሚን ‹‹ኤ›› የበለጸጉ ምግቦች የሚባሉት እንደ ጉበት፣ካሮት፣ ስኳር ድንች፣ጎመን፣ቃሪያ፣ሰላጣ፣እንጆሪ፣ማንጎ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ከፍተኛ የቫይታሚን ‹‹ኢ›› መጠን ካላቸው ምግቦች መካከል ቆስጣ፣የሱፍ ቆሎ ፣አቮካዶ፣ አሳ፣ የ ወይራ ዘይት ፣ስኳር ድንች ፣ጥቁር እንጆሪና ማንጎ ይገኙበታል፡፡

ከምግብ በተጨማሪ የዓይን ጤንነት ለመጠበቅ በቀን በአማካይ 1- 2 ሊትር ወሀ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
2) ለጤና ጠንቅ ከሆኑ ልማዶች እራስን መጠበቅ
ሲጋራ ማጨስ በሲጋራው ጭስ ውስጥ የሚገኙ መርዛማ ኬሚካሎች በዓይን ሌንስ ፣ሰገነተ እይታ ፣እይታይ ነርቭና የዓይን ደም ስሮች ላይ ጉዳት ስለሚደርሱ እይታን ይጎዳሉ፡፡ ባጠቃላይ ሲታይ እድሜ እየገፋ ሲሄድ የሚያጨሱ ሰዎች ከማያጨሱ ሰዎች በሁለት እጥፍ በበለጠ እይታቸዉን ማጣት እድል አላቸዉ ፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የአልኮል መጠጥ አብዝቶ መውሰድ ሌንስን፣ ሰገነተ እይታንና እይታ ነርቭን ሊጎዳ የሚችል የኬሚካል ውህድ ስለሚፈጥር የአልኮል መጠጥ መቀነስ ከተቻለም ማቆም ለ ዓይን ጤና ድርሻው የጎላ ነው፡
3) ዓይንን ከአደጋ መጠበቅ
አይንን ለአደጋ ከሚያጋልጡ ነገሮች መካከል የስራ ቦታና የስራ ዘርፎች ( ፋብሪካዎች፣ የእርሻ ልማት ፣ የመኪና ጋራጅ፣ የግንባታ ቦታዎች ፣የድንጋይ ፈለጣ ፣ የአትክልተኛነት ስራ ወዘተ……) ከዚህ በተጨማሪ ለብርሃን ጨረር መጋለጥ በዓይን የተለያዩ ክፍሎች ላይ ጉዳት ስለሚያደርስና ለሌሎች ችግሮች ስለሚያጋልጥ ከጨረርና ጸሃይ ተከላካይ የሆኑ መነጽሮችን መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

4) የቴክኖሎጂ ምርቶች አጠቃቀም ማስተካከል
ረዘም ላለ ጊዜ የቴክኖሎጂ ምርቶች ላይ( ኮምፒዩተር፣ ታብሌት ፣ሞባይል) በሚያሳልፉበት ጊዜ የቅንድብ መርገብገብ ከመደበኛ ጊዜ ስለሚቀንስ በቂ የእንባ ስርጭት ስለማይኖር የአይን ድርቀት ፣ የእይታ ብዥታና የዓይን ዝለት ያስከትላል፡፡ እነዚህ ችግሮች በቀን ከ 2ሰዓት በላይ ኮምፒዩተር ላይ በሚያሳልፉ ሰዎች ላይ ጎልቶ ይታያል ፡፡
ኮምፒዩተር መጠቀም ግድ ከሆነ መደረግ ያለባቸዉ ጥንቃቄዎች፡-
• የኮምፒዩተር አቀማመጥን ማስተካከል.
• የኮምዩተሩን ማሳያ የቀለም ስብጥርና ደማቅነት ማስተካከል
• ነጸብራቅ የሚከላከሉ የሞኒተር ልብሶችን መጠቀም
• ሞኒተሩን ከአቧራና ከጣት አሻራ የጸዳ ማድረግ
• የፊደላትን መጠን ከፍ ማድረግና ሞኒተሩን ብዙ ነገር በመከፋፈት አለማጨናነቅ
5.መደበኛ የአካለ ብቃት እንቅስቃሴ
ዓይናችንን ጤናማ ሆኖ ለመቆየትና ስራውን በተገቢው ሁኔታ ለማከናወን ከፍተኛ የኦክስጅን መጠን ያስፈልገዋል፡፡ ስለሆነም በደም ዉስጥ የሚገኘዉን የኦክስጅን መጠን የሚጨምር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ(ኤሮቢክስ) ለእይታ ነርቭ ህዋስ የሚያስፈልገዉን ኦክስጅን ከመጨመር ባለፈ የዓይን ግፊትን ለመቀነስ ይረዳል፡፡
6) መደበኛ የዓይን ምርመራ ማድረግ
መደበኛ የዓይን ምርመራ ማድረግ ችግሮችን በቶሎ ለማወቅና ለመታከም ይረዳል፡፡

ምንጭ: ዶክተር አለ(Doctor Alle)

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.