የወሎ ምድር ነዳጅ አፈለቀ እየተባለ ነው፤ ምን ያህል እውነት ነው?

በወሎ ነዳጅ ፈለቀ ተባለ፡፡ ወሬው በማኅበራዊ ሚዲያ ሞልቶ ፈሰሰ፡፡ አንዳንዶች ዜናውን በምሥልም በሰው ምስክርም አስደግፈውታል።

ቢቢሲ አማርኛ ወደ ደቡብ ወሎ ለገሂዳ ወረዳ በደወለበት ጊዜ አቶ ተመስገን አሰፋን አገኘ፡፡ ተመስገን የወረዳው የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ነው፡፡

በአካል ቦታው ድረስ ሄዶ ነገሩ ሐቅ ስለመሆኑ አረጋግጧል፤ ነዳጁ ዓለት ሰንጥቆ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ‘መቸላ’ ወንዝ እንደሚገባም ታዝቧል።

በእርግጥ አቶ ተመስገን የተመለከተው ባዕድ ፈሳሽ ነዳጅ ነው?

“ማህበረሰቡ በፕላስቲክ ጠርሙስ ነዳጅ እየቀዳ ይወስዳል”

የቪዲዮና የፎቶግራፍ ማስረጃዎችን በጥንቃቄ የያዘው ተመስገን ነዳጅ ስለመሆኑ አንድ ሁለት እያለ ምስክር ይቆጥራል።

“ከሚፈልቀው ነዳጅ ጨልፈን ክብሪት ስንለኩስበት ይቀጣጠላል” አንድ፤

“ነዋሪዎች ነዳጁን በፕላስቲክ ጠርሙስ እየቀዱ ይወስዱ ነበር” ሁለት፤

“ገና ከሩቁ የነዳጁ ሽታ ይጣራል” ሦስት፤

“ለሺ ዓመታት የነበረ ነው”

የነዳጅ ክምችቱ ይገኝበታል የተባለው ሥፍራ በወረዳው 0-10 ቀበሌ ልዩ ቦታው ጎራና ት/ቤት አቅራቢያ ነው። አካባቢው ቆላማና ቁልቁለታማ በመሆኑ ከወረዳው ከተማ ወይን አምባ በእግር ለመድረስ አንድ ሰዓት ይወስዳል። ይሄ ወጣ ገባ መልክአ ምድር ለነዳጁ ጎብኚዎች ብቻ ሳይሆን ለነዳጅ አውጪዎችም ፈተና ሳይሆን አልቀረም። ስለዚህ ጉዳይ ወደ ኋላ ከባለሙያ ጋር እንመለስበት።

የወሎ ሰው በድንገተኛ አግራሞት ሲያዝ ‘አጃኢብ’ ነው ይላል፤

ለመሆኑ የሚመለከተው የፌዴራል መንግሥት ይህንን ‘አጃኢብ’ ሰምቶት ይሆን?

በኢፌድሪ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሚካኤል መንገሻ “ነገሩ ትንሽ ተጋኖ ይሆናል እንጂ ነዳጅስ ነዳጅ ነው” ካሉ በኋላ “ግን እኮ ይሄ አዲስ ነገር አይደለም” ይላሉ።

“ነዳጁ የዐለት ግድቡን ጥሶ አካባቢውን አጥለቅልቆታል” የሚለውን የማኅበራዊ ሚዲያ ወሬን ነው ‘ተጋኗል’ ያሉት፡፡

“ታዲያ ያልተጋነነው እውነት ምንድነው?” አልናቸው፤ አቶ ሚካኤልን፡፡

“የታየው ነዳጅ ነው፡፡ የኛም ባለሙያዎች ሁለት ሦስት ጊዜ ሄደው ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡”

ታዲያ ምንድነው የሚጠበቀው? ለምን አይወጣም…?

ዶ/ር ቀጸላ ታደሰ በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው፡፡ ይህንኑ ጥያቄ አነሳንላቸው፤ ‹‹እንደምትለውማ ቢሆን እኛው በዶማ ቆፈር ቆፈር አድርገን አናወጣውም ነበር?” ሲሉ ከቀለዱ በኋላ በደቡብ ወሎ የታየው ዘመን ያስቆጠረ እንጂ አዲስ ክስተት እንዳይደለ ያብራራሉ፡፡

የኢትዯጵያ የነዳጅ ፍለጋ እንክርት 70 ዓመት አልፎታል። እስከዛሬም አመርቂ ውጤት አልተገኘም። ከኦጋዴን በስተቀር።

ያም ሆኖ በወሎ ዙሪያ ላለፉት አሥር ዓመታት የነዳጅ ፈላጊ ኩባንያዎች ጠፍተው አያውቁም፡፡

ዶ/ር ቀጸላ ነገሩን ከሥር መሠረቱ ያስረዳሉ።

ለነዳጅ ፈላጊዎች ፍቃድ ሲሰጥ መጀመሪያ ለአራት ዓመት (Initial Exploration License) ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያ ይበል የሚያሰኙ ሁኔታዎች ሲታዩና የይራዘምልን ጥያቄ ሲያቀርቡ ተጨማሪ ሁለት-ሁለት ዓመት ይፈቀድላቸዋል፡፡ በድምሩ ስምንት ዓመት መሆኑ ነው፡፡

በእነዚህ የተራዘሙ የፍለጋ ዓመታት ታዲያ አንድ ኩባንያ ዝርዝር ጥናት አድርጎ፤ የከርሰ ምድር ናሙናዎችን ወስዶ አጥጋቢ ሲሆን ብቻ ወደ ቁፋሮ ሊገባ ይችላል፡፡ ያም ሆኖ የነዳጅ ክምችቱ ኖሮ ነገር ግን ነዳጁ ቢወጣ ለረዥም ዓመታት የማይዘልቅ ሲሆን፣ ወይም በሌላ የአዋጪነት ምዘና ፍለጋው ባይሰምር ለፍለጋ የወጣው ወጪ ቀልጦ ይቀራል፡፡

ይህ ወጪ በሁኔታዎች ተለዋዋጭ ቢሆንም ቀላል የሚባል አይደለም። በትንሹ ሩብ ቢሊዮን ብር ጠራርጎ ይወስዳል።

የወሎ ምድር ነዳጅ አፈለቀ እየተባለ ነው፤ ምን ያህል እውነት ነው?Image copyrightTEMESGEN ASSEFA

በዚሁ የደቡብ ወሎ ነዳጅ ፈለቀ በተባለበት ሥፍራ ፋልከን የሚል ስም ያለው አንድ የእንግሊዝ ኩባንያ በፍለጋ ዘለግ ያሉ ዓመታትን ተንከራቷል። የሙከራ ቁፋሮ ለማድረግም በሦስት ማዕዘናት ዳስ ጥሎ ነበር፡፡ በፋይናንስ ምክንያት አልቀናውም፡፡

“አንዱ ችግር የጂኦሎጂውና የመልክዓ ምድሩ ምቹ አለመሆን ነው። ረቂቅ ቴክኖሎጂንም ይጠይቃል። አካባቢው ክምር አለው። እንደ ሶማሌ አካባቢ ዝርግ መሬት አይደለም። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ ካፒታል ይጠይቃል። ፋልከን ያን ያህል ካፒታል አልነበረውም። ከአራት ዓመት በፊት ከአካባቢው ነቅሎ የወጣውም ለዚሁ ነው።

ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ውል ያቋረጠበት ይህ ኩባንያ በአካባቢው ትምህርት ቤት ሳይቀር አስገንብቶ እንደነበር አቶ ሚካኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በቅርቡ ነዳጅ ፈላጊ ኩባንያ ይገባል”

ዶ/ር ቀጸላና የሥራ ባልደረቦቻቸው ይህን የወሎ ክፍል በብዙ ተመላልሰውበታል። ጥናትም ሠርተውበታል።

“ነዳጅ መፍለቁን እያየን ቸል ማለት ነው በቃ?” አልናቸው። “ገንፍሎ መውጣቱስ የሚነግረን ምንድነው?”

“እርግጥ ነው ችላ ተብሎ የሚታለፍ አይደለም። መንግሥት ያውቀዋል፤ ባለሙያዎች ጥናት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ። ነገር ግን አንድ ቦታ ፈለቀ ማለት ነዳጅ አለ ማለት አይደለም። ከብዙ ማይል ርቀት እየመጣ ሊሆን ይችላል።”

ይህ ግን ምን ማለት ይሆን?

መሬቱ በተለያየ ምክንያት በአንዳች ቦታ ስንጥቅ ይኖረዋል፤ ስንጥቅ አግድም ሊሆን ይችላል፡፡ ያንን ተከትሎ ነዳጅ ሊፈልቅ ይችላል። ነዳጁ ከዚያ ሥፍራ ስለመኖሩ መናገር የሚቻለው ግን በብዙ ጥናት ብቻ ነው።

ዶክተር ቀጸላ ነገሩ ውስብስብ እንደሆነ ከገለጹ በኋላ ለማብራራት ሞክሩ። የጂኦሎጂ ሁኔታ ማለት ‘በዘቀጤ ዐለት’ የተሠራ ሊሆን እንደሚችል፣ እሳተ ጎመራ የወለደው ዐለት ወይም ሁሉንም ያቀላቀለ ዐለት ሊኖር ወይም በዘመናት የተቀየጠ እነዚህን ሁሉ ያቀላቀለ የጂኦሎጂ ዓይነት በቦታው ሊኖር እንደሚችል ዘረዘሩ።

“ይህ በሙሉ ሳይጠና [ክምችቱ] ትንሽ ነው ትልቅ ነው አይባልም።”

ደቡብ ወሎ ሰሞኑን ስለታየው ሲናገሩም “ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደሚባለው አይደለም፤ አገር እየበከለ ነው የሚባው ዉሸት ነው፤ ሆኖም በቅርቡ አዲስ ኩባንያ በወሎ ፍለጋ ሊጀምር በዝግጅት ላይ ነው።”

“አንዳንዴ ዕድልም ይጠይቃል. . .”

የነዳጅ ምልክቶች ከታዩ በኋላ ምን ያህል ጊዜን ይወስዳል?

አቶ ሚካኤል “በብዙ ሁኔታዎች ይወሰናል” ይላሉ። የኩባንያው የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ብቃት፤ የአካባቢው የዐለት አፈጣጠር፤ ጠቅላላ መልክዓምድር፣ አዋጪነት. . .ወዘተ ጊዜውን ሊወስኑት ይችላሉ።

ዶ/ር ቀጸላ በበኩላቸው የተፈጥሮ ጋዝም ሆነ ነዳጅ በጥምረት አልያም ለየብቻ ሊገኙ እንደሚችሉ ካወሱ በኋላ ሆኖም ሥራው ብዙ ሚሊዮን ዶላር እና ውስብስብ ቴክኖሎጂን እንደሚጠይቅ ያሰምሩበታል።

“አንዳንዴ ዕድልም ሳይጠይቅ አይቀርም።”

የወሎው ክስተት ግን ለአገሪቱ አዲስ አይደለም ይላሉ። ምዕራብ ኦጋዴን ደርከሌ፣ ገናሌ አካባቢ፣ በምሥራቅ ደግሞ ገለምሶ ልክ እንደ ወሎ ሁሉ ነዳጅ ፈልቆ ያውቃል። እንደ ኦጋዴን የተፈተሸ የኢትዮጵያ ክፍል ባይኖርም።

እስከአሁን አገሪቱ የቀናትም በኦጋዴን ተፋሰስ በኩል ነው፤ በሂላላና በኤልኩራን።

ለጊዜው ግን ወሎ የጠራ ነዳጅ ለማግኘት ዓመታትን መጠበቅ ሳይኖርባት አይቀርም።

 

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.