ጠ/ሚ ዶክተር አብይ በ50 ቢሊየን ብር የሚከናወነውን የለገሃር የተቀናጀ መንደር ግንባታ በይፋ አስጀመሩ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የለገሃር የተቀናጀ መንደር ግንባታን በዛሬው እለት በይፋ አስጀመሩ።

በማስጀመር ስነ ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር የተቀናጀ መንደር ግንባታው አዲስ አበባን እንደ ስሟ ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ የተያዘው እቅድ አካል ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ነዋሪዎች ሳያፈናቅል ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ የሚገነባ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከአጠቃላይ ፕሮጀክቱ መንግስት 27 በመቶ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በሚገነባበት ወቅትም በአካባቢው የሚኖሩ 1 ሺህ 600 ያክል ዜጎች አካባቢያቸውን ሳይለቁ በ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የተሻለ መኖሪያ ቤት እንደሚገነባላቸውም አስረድተዋል።

የፕሮጀክቱ ግንባታም የለገሃር አካባቢን ታሪካዊ ይዘት ሳይለቅ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፥ በቀጣይም መሰል የመንደሮች ግንባታ እንደሚኖርም ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ውስጥ በአጠቃላይ ከ4 ሺህ በላይ የመኖሪያ አፓርታማዎች የሚገነቡ ሲሆን፥ ይህም የከተማዋን የቤት እጥረት ለማቃለል ይረዳልም ነው ያሉት።

ዛሬ በይፋ የተጀመረው ፕሮጀክት አጠቃላይ ግንባታ ከ5 እስከ 7 አመት የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ የመንደሩ የመጀመሪያ ሞል ግንባታም በሶስት አመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።

መቀመጫውን አቡ ዳቢ ባደረገው ኤግል ሂልስ ኩባንያ የሚገነባው ይህ መንደር 50 ቢሊየን ብር ወጪ ሲደረግበት፥ ለ25 ሺህ ሰው የስራ እድል ይፈጥራል ነው የተባለው።

በውስጡም ሶስት ዘመናዊ ባለ 4 እና 5 ኮኮብ ሆቴሎችን፣ የመኖሪያ አፓርታማ፣ የንግድ ስፍራዎች፣ የመዝናኛ ስፍራ እንዲሁም ግዙፍና ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ይኖረዋልም ነው የተባለው።

በመጨረሻም በተለይም ወጣቱ በባለቤትነት መንፈስ እንዲንቀሳቀስም ጥሪ አቅርበዋል።

ግንባታውን የሚያከናውነው ኤግል ሂልስ ኩባንያ ሊቀ መንበር ሙሃመድ አላባር በበኩላቸው፥ ኩባንያቸው ከሁለት አስርት አመታት በላይ በመሰል የግንባታ ዘርፎች የካበተ ልምድ እንዳለው አንስተዋል።
አሁን የተረከቡን ፕሮጀክትም የአካባቢውን ታሪካዊነት በጠበቀ መልኩ፥ የቴክኖሎጅ እና የዕውቀት ሽግግርን በሚያስፋፋ መልኩ ይገነባልም ብለዋል ሊቀ መንበሩ።
የመንደሩ ግንባታም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ዘመናዊና ምቹ የመኖሪያ መንደር እንዲገነባ ባሳዩት ፍላጎት መሰረት የሚከናወን መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.