በቻይና ሰው ሰራሽ የማሰብ አቅም ያለው ዜና አቅራቢ ሮቦት ተሰራ

የዓለማችን ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት በሆነችው ቻይና ሰው ሰራሽ የማሰብ አቅም ያለው ዜና አቅራቢ ሮቦት መሰራቱ ተገለጸ፡፡

ሮቦቱ የመንግስት መገናኛ ብዙኀን በሆነው ሽንዋ ውስጥ በዜና አቅራቢነት ስራ መጀመሩም ተሰምቷል፡፡

ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው ሙከራ በመንደሪንና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች በተሳካ ሁኔታ ዜና ማቅረብ መቻሉ ተነግሯል፡፡

ሽንዋ እንዳለው ከሆነ ሮቦቱ ዜና አቅራቢ ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ ስራውን በይፋ መጀመሩን በትዊተር ገጹ ይፋ አድርጓል፡፡

ይህ ሰው ሰራሽ የማሰብ አቅም የተላበሰው ሮቦት ታዲያ ዜናዎችን ለተመልካቾች በማንበብ ጭምር እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

የዜና ተቋሙ ከሮቦቱ የስራ ሁኔታጋር በተያያዘም ለ24 ሰዓታት ያለእረፍት በድረ-ገጾቹና በማህበራዊ ሚዲያ አድራሻዎቹ ላይ እንደሚሰራ ጠቅሶ፥ ይህም ወጪን እንደሚቆጥብለት አስታውቋል፡፡

እንዲሁም ሰበር ዜናዎች በሚኖሩበት ወቅት ጊዜውን ሳያስተጓጉሉ በፍጥነት ለተመልካቾች ዜናዎችን የማድረስ ልዩ አቅምም አለው ብለዋል፡፡

ዜና አቅራቢው ሮቦት መነሻ ተደርጎ የተሰራው በተቋሙ ውስጥ የሚሰራን አንድ ዜና አቅራቢ መላ እንቅስቃሴን በማስመሰል መሆኑ ተነግሯል፡፡

ሆኖም አንዳንድ ባለሙያዎች ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ ሮቦቱ የሚያቀርበውን ዜና ማየት እንደሚያዳግት ጠቅሰው፥ ይህም ሰዋዊ የሆነውን የዜና አቀራረብ መላበስ ባለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡

በርግጥ አስተያየት ሰጪዎቹ እንደመጀመሪያ ፈጠራነቱ ግኝቱን ያደነቁ ሲሆን፥ በሂደትም መሻሻሎች ታክለውበት ተወዳጅ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.