የአስር ደቂቃ እንቅስቃሴ የማስታወስ ችሎታን እንዴት ይጨምራል?

አጭር የእግር ጉዞም ይሁን፣ የማርሻል አርትስ ልምምድ፤ ቢያንስ ለአስር ደቂቃ ማንኛውንም አይነት የአካል እንቅስቃሴ ካደረጉ የማስታወስ ችሎታዎን በፍጥነት መጨመር ይችላሉ።

በካሊፎርንያ ዩኒቨርሲቲ ጥናት የሚያካሂድ የተመራማሪዎች ቡድን በጥናቴ ደረስኩበት እንዳለው ሌላው ቢቀር በቀን ለአስር ደቂቃ ቀለል ያለ ያአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የዓዕምሯችንን የሥራ ሂደት ለማነቃቃት በቂ ነው።

ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው የሰውነት እንቅስቃሴ በዓዕምሯችን ላይ ያለውን አዎንታዊ ተጽዕኖ ለማረጋገጥ ”ኤምአርአይ” የተባለውን የህክምና መሳሪያ የተጠቀሙ ሲሆን፤ በርካታ ሰዎች ላይም ሙከራ ተደርጓል።

ምንም አይነት የሰውነት እንቅስቃሴ ያላደረጉ ሰዎችን እንቅስቃሴ ካደረጉ ሰዎች ዓዕምሮ ጋር ሲነጻጸር እንቅስቃሴ ያደረጉት ሰዎች ጭንቅላት በጣም ፈጣንና ውጤታማ በሆነ መልኩ መልእክቶችን ይለዋወጣል።

ተመራማሪዎቹ ባሳተሙት የጥናት ጽሁፍ ላይ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ ሶስት ወሳኝ ጥቅሞች አሉት።

  1. ሊረሱ የሚችሉ ነገሮችን የማስታወስ አቅምን ይፈጥራል እንዲሁም በፈጥነት የማሰላሰል ብቃትን ይጨምራል
  2. ”ሂፖካመስ” የሚባለው የዓዕምሯችን ክፍል በፈጣነት እንቅስቃሴ ይጀምራል
  3. ዓዕምሯችን ከመላው የሰውነታችን ክፍል ጋር የሚያደርገው የመልዕክት ልውውጥ የተቀላጠፈ ይሆናል
የሰውነት እንቅስቃሴ የሚሰሩ አዛውንቶችImage copyrightGETTY IMAGES

ይህ የተመራማሪዎች ቡድን ባደረገው ጥናት የአስር ደቂቃ እንቅስቃሴ ማድረግ አይደለም ለሰው ልጆች የአይጦችን የማስታወስ ችሎታ እንደሚጨምረው ጠቁሟል።

የሙከራውን ውጤታማነት ለማረጋገጥ በጥናቱ የተሳተፉት 36 በጎ ፈቃደኞች የማስታወስ ችሎታቸው ቀድሞ ለማወቅ ከጥናቱ በፊት እንዲፈተሽ ተደርጓል።

በጎ ፈቃደኞቹ 186 አይነት እቃዎች፣ ፍራፍሬዎችን እና ሌሎች መገልገያዎችን ምስል እንዲመለከቱ የተደረገ ሲሆን፤ ቀጥሎም ተጨማሪ 256 ምስሎችን እንዲመለከቱ ተደርገው ምን ያህሉን እንደሚያስተውሱ ተፈትሸዋል።

በሚያስገርም ሁኔታ ለአስር ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት የጥናቱ ተሳታፊዎች እንቅስቃሴ ካላደረጉት በተሻለ የተመለከቷቸውን ምስሎች ማስታወስ ችለዋል።

ምንም እንኳን የአካል ብቃት እነቅስቃሴ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ቢታወቅም አዲሱ የምርምር ውጤት ግን ቢያንስ ለአስር ደቂቃ እንቅሳቄ የማድረግ አስገራሚ ጥቅሞችን ያብራራ ነው።

ከዚህም በተጨመሪ የሰውነት እንቅስቃሴ ከእድሜ መጨመራ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ የማስታወስ ችግሮችን ለማከምና ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ተብሏል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

2 Comments

Comments are closed.