ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ድጋፍ ለመግለጽ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ቦምብ በማፈንዳት ተጠርጥረው በተያዙ ግለሰቦች ላይ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሽብርተኝነት ክስ መሰረተ።

በሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተፈፀመው ጥቃት የሙሳ ጋዲሳና ዮሴፍ አያሌው የተባሉ ግለሰቦች ህይወታቸው ማለፉንና ከ163 በላይ ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱ በክሱ ተገልጿል።

ከተፈፀመው ከዚህ የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ተይዘው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን ከእነዚህም መካከል አምስቱ ላይ በአቃቤ ህግ ዛሬ ክስ ተመስርቶባቸዋል።

አቃቤ ሕግ ቦምብ በማፈንዳት የወንጀል ክሱ የተመሰረተባቸው አምስቱ ተጠርጣሪዎች ጌቱ ግርማ፣ ብርሃኑ ጃፈር፣ ጥላሁን ጌታቸው፣ ባህሩ ቶላ እና ደሳለኝ ተስፋዬ ናቸው።

የጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው አንደኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ ከሁለተኛ ተከሳሽ ጋር ሱሉልታ ላይ በመገናኘት ሰልፉን የጠራው ገለልተኛ ወገን ሳይሆን ኢህአዴግ ነው ኤችአር 128 የተባለውን በአሜሪካ ኮንግረስ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ያደርጋል የሚል ምክንያቶችን በመግለጽ ቦምቡን በመወርወር እንዲበተን እናድርግ በማለት እንዲዘጋጁ አድርጓል።

ለሦስተኛ ተከሳሽ ደውሎም ቦምብ የሚወረውር ሰው አንዲፈልግ ተልዕኮ መስጠቱ በክሱ ተገልጿል፡፡

ሌሎችም ተከሳሾች በቡድን በመደራጀት ለጊዜው በቁጥጥር ስር ባልዋሉ ግለሰቦች ጋር በመተባበር በተለያየ መንገድ ቦምቡን ለመወርወር ሰዎችን በመመልመልና በሌሎችም ጉዳዮች ተሳታፊ እንደሆኑ ክሱ አትቶ በሽብርተኝነት ድርጊትም ወንጅሏቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የቦብ ፍንዳታውን የወንጀል ድርጊት ያቀነባበረችው በኬንያ ናይሮቢ የምትገኝ ገነት ታምሩ (ቶለሺ ታምሩ) የምትባል መሆኗን፣ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል፡፡

ምንጭ: ቢቢሲ