NEWS: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለኖቤል ታጭተዋል?

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ በጥቂት ወራቶች ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ብቻም ሳይሆን የኖቤል ሽልማት እንዲያገኙም ጭምር ዘመቻ እየተደረገላቸው ነው።

የኢትዮጵያ ዜጎችን ጨምሮ ከዚያም ባሻገር ዐብይ አሕመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያሉትን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ሽልማቱ ይገባቸዋል የሚሉ ድምጾች በርክተዋል።

በተለይም ከኤርትራ ጋር የጀመሩት የሰላም ጉዞ በደጋፊዎቻቸው የሽልማት “ይገባዎታልን” ዘመቻ ከፍ ብሎ ተሰምቷል።

• “አካል ጉዳተኛ መሆኔ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ አድርጎኛል”

• ‘ገዳይ ጨረር’ እንዴት ራዳርን ለመፈብረክ ረዳ?

እንደ ጎርጎሪዮሳዊያኑ አቆጣጠር በሐምሌ 23 የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ አማካሪ የነበሩት ኸርማን ኮኸን በትዊተር ገጻቸው ላይ የሚከተለውን ጻፉ- “በሞያ ዘመኔ ለመጀመርያ ጊዜ አንድ ሰው ለኖቤል እጩ ማድረጌ ነው፤ ያ ሰው ዐብይ አሕመድ ነው፤ ለአገሩ አሳታፊ ዲሞክራሲን ካመጣ መላው የአፍሪካ ቀንድ ወደተሻለ ቀጠና ይሸጋገራል።”

ይህ የኸርማን ጄ ኮኸን ሐሳብ ብዙዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተጋርተውታል፣ አጋርተውታል።

ኖቤል በዘመቻ ይገኛል?

በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እንደሚታየው ከሆነ ዶክተር ዐብይ ለእጩነት፣ አንዳንዴም ለአሸናፊነት ጫፍ ደርሰዋል። የሚያስፈልጋቸው የሕዝብ ድምጽ ነው የሚሉ መረጃዎች በስፋት ሲዘዋወሩ ሰንብተዋል።

ለመሆኑ የኖቤል የሽልማት ሥርዓት እንዲህ አይነቱን አሠራር ይከተላል? እነማን መጠቆም ይችላሉ?

ከኖቤል ሽልማት ይፋዊ ድረ-ገጽ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ የኖቤል እጩዎች ጥቆማ የሚሰጠው በበቁ ሰዎች ብቻ ነው።

እነዚህ የበቁ ጠቋሚዎች የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው።

• የአንድ ሉአላዊት አገር የካቢኔ አባላት ወይም የአገር መሪዎች

• የሄግ የግልግል ፍርድ ቤት ወይም የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አባላት አልያም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወይም በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ ፕሮፌሰሮችና ተባባሪ ፕሮፌሰሮች

• ቀደም ብለው ኖቤል ያሸነፉ ሰዎች ወይም ያሸነፉ ድርጅቶች የቦርድ ሰብሳቢዎች

• የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የቀድሞም ሆኑ የአሁን አባላት

• የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ አማካሪዎች ናቸው።

ከላይ በተዘረዘሩት አባላት እጩው ሲቀርብ ነው ሕጉን ተከተለ የሚባለው። አንድ ሰው ራሱን እጩን አድርጎ ማቅረብ አይችልም።

የኖቤል ኮሚቴ አምስት አባላት ያሉት ሲሆን የኮሚቴው አባላት የሚሰየሙት በኖርዌይ ፓርላማ ነው።

የኖቤል የሰላም ሽልማትን ካገኙ ሰዎች መካከል ማንዴላ አንዱ ናቸውImage copyrightAFP
አጭር የምስል መግለጫየኖቤል የሰላም ሽልማትን ካገኙ ሰዎች መካከል ማንዴላ አንዱ ናቸው

ዐብይ አሕመድ ስለመጠቆማቸው ማን ሊነግረን ይችላል?

ኮሚቴው የእጩዎችንም ሆነ የጠቋሚዎችን ማንነት ለሚዲያም ሆነ ለእጩዎቹ በምንም መልኩ አይገልጽም። ማን ማንን ጠቁመ፣ እነማን እንዴት ተመረጡ ወይም ተጠቆሙ የሚሉ መረጃዎች የሚወጡት ሽልማቱ ከተካሄደ ከ50 ዓመታት በኋላ ብቻ ነው። ይህ ማለት ዐብይ አሕመድ የ2018 የኖቤል እጩ ስለመሆናቸው እርግጡን የምናውቀው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2060 ይሆናል።

የኖቤል ኮሚቴው የጊዜ ሰሌዳ

መስከረም፡– በፈረንጆች መስከረም (ሴፕቴምበር) የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ እጩዎችን ለመቀበል ይሰናዳል። እጩ የመቀበሉ ሥራ ለቀጣይ ስድስት ወራት ይጸናል። እጮዎቹን መጠቆም የሚችሉት ከላይ የተዘረዘሩት ብቁ ጠቋሚ የተባሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ብቻ ናቸው።

የካቲት በየካቲት የእጩዎች መቀበያ ጊዜ ያበቃል። ከየካቲት 1 በፊት ያልተጠቆመ በዚያ ዓመት እጩ መሆን አይችልም።

መጋቢት፡-ኮሚቴው የእጮዎችን ዝርዝር ያቀርባል። ከእጮዎቹ ውስጥ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑትን ብቻ ለተጨማሪ ማጣሪያ ይቀርባሉ።

ጥቅምት፦ በጥቅምት መጀመርያ ኮሚቴው አሸናፊውን በድምጽ ብልጫ ይመርጣል። ይግባኝ የማይባልበት ምርጫ ነው ታዲያ።

በታኀሳስ፦ 10 (በፈረንጆቹ) በኦስሎ ኖርዌይ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ይካሄዳል።

የጊዜ ሰሌዳውና ዐብይ አሕመድ

የኖቤል ሽልማት ከአንድ ዓመት ዘለግ ያለ ጊዜን የሚወስድ ሂደት ነው። ኾኖም ጥቆማ የመቀበያ ጊዜ ከፈረንጆች መስከረም ጀምሮ ለ6 ወራት የሚዘልቅ ነው። ይህ እንግዲህ መጪውን የመስከረም ወር ሳይሆን የ2017ቱን ወር አንድ ብሎ የሚጀምር ነው።

የእጩ መስኮቱ ከተዘጋ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት ዐብይ አሕመድ ቢያንስ የ2018 የኖቤል ሽልማት እጩ የመሆናቸው ነገርን አጠያያቂ ያደርገዋል። ምናልባት የኖቤል ኮሚቴው በመጨረሻዎቹ ጊዜያት እጩ የመጨመር ሥልጣን ስላለው ያ ተግባራዊ ከሆነ ጠባብ እጩ የመሆን እድል ሊኖራቸው ይችላል።

አልያ ግን ከወር በኋላ ጀምሮ ለ6 ወራት በሚጸናው የ2019 የኖቤል ሽልማት ለመካተት ካልሆነ በስተቀር፤ ዐብይ አሕመድ ከዚህ ውጭ በማንኛው አካል የሚደረገው ዘመቻ በኮሚቴው ምርጫ ሂደት ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማያደርግ ይታወቃል።

ለዓለማችን የላቀ አስተዋፅኦን ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት አጀማመር።

ተጨማሪ መረጃዎች

ይህ በእንዲህ እያለ በታሪክ ከፍተኛው የእጩ ቁጥር የቀረበው በ2016 ነበር። በዚያ ጊዜ የተመዝጋቢ እጩዎች ቁጥር 376 ሲሆን የዘንድሮውም ቀላል የሚባል አይደለም። 330 እጩዎች ቀርበዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዐብይ አሕመድ ይገኙበታል ወይ ነው ጥያቄው።

ዘንድሮ ከቀረቡት ከነዚህ እጩዎች ውስጥ 216 የሚሆኑት ግለሰቦች፣ 114ቱ ደግሞ ድርጅቶች ናቸው።

ይህ ሽልማት በ1901 ጀምሮ ለ96ኛ ጊዜ ተሰጥቷል።

ይህንንም ሽልማት 86 ግለሰቦች ወንዶች 16 ሴቶች እና 23 ድርጅቶች አሽንፈዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.