NEWS: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በአሜሪካ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሰጡት ምላሽ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት የሚገኙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን በትልቅ መሰብሰቢያ ውስጥ አግኝተው ከነጋገሩ በኋላ በተዘጋጀ የእራትና የውይይት መረሃ ግብር ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት ባለፉት አራት ዓመታት እንቅልፍ ተኝተው እንደማያውቁ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለፉ አስታውሰው በተለይ ከአራት ወራት በፊት የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው እንደነበርም ተናግረዋል።

የእስር ማዘዣው ከየትኛው ወገን እንደመጣ በግልፅ ባይናገሩም ከሀገር እንዲወጡ የሚያስገድዱ ጫናዎች እንደነበሩም ጠቁመዋል። “እኛም አንወጣም ብለን እዚያው የሚመጠውን ሁሉ ለመጋፈጥ ቆርጠን ቆይተናል ምክንያቱም ከሃገር የወጡ አልተመለሱም። ለዚህም ነው እዚህ ቦታ ላይ ልንደርስ የቻለው” ብለዋል።

• ዶክተር ብርሃኑ ነጋ መቼ አገር ቤት ይገባሉ?

• 40 ታጣቂዎች በመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተያዙ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉዞ ተጠናቀቀ

በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከታዳሚው ለቀረቡላቸው የተለያዩ ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

የሶማሌ ክልልን በተመለከተ

በኢትዮጵያ ያሉት ሶማሌዎች ብቻ ሳይሆን ሞቃዲሾ ያለውም ጭምር ዴሞክራሲን እንዲተገብርና ከኢትዮጵያዊያንና በተለይ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ተሳስሮ መኖር አለበት ብለን በጽኑ እናምናለን በማለት ጀምረዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ክልሉ መሪ ያስፈልገዋል፤ ክልሉ የልብ አንድነት ያስፈልዋል። ብዙዎቻችሁ ላታስተውሉት ትችላላችሁ ግን አፍሪካ በብዙ ጅብ መንግሥታት የተያዘች አህጉር ናት። እነዚህን መንግሥታት ከጎረቤት አስቀምጠን ኢትዮጵያ ላይ ዴሞክራሲ፤ ኢትዮጵያ ላይ ሰላም ማምጣት አይቻልም።

አፍሪካ የሚገባትን ክብር እንድታገኝ በጋራ መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በቂ ጭንቅላት አላት፤ 100 ሚሊዮን ምርጥ ጭንቅላት። ይህንን በማውጣት መስራት ያስፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የሶማሌ ክልልን በተመለከተ በመንግስት በኩል ሪፎርም እየሰራ እንደሆነና ህዝቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።

ዶክተር ብርሃኑ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ምን ተወያዩ?

• ያልተነገረለት የኮንሶ ጥያቄ

በኦሮሞና በሶማሌ መካከል የተነሳውን ግጭት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ “ኦሮሞና ሶማሌ አንድ ቤተሰብ ናቸው፤ ስለዚህ ማንም ምንም አለ አብሮ ተጋግዞ መስራት ብቻ ነው የሚያዋጣው ብለዋል።”

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነትን በተመለከተ

”በመጀመሪያ ትኩረተ የሰጠነው ዋነኛው ነገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር ላይ ነው። ለዚህም ነው በፍጥነት የአውሮፕላን ጉዞ ያስጀመርነው፤ የሚያገናኙንን መንገዶች እየጠገንን ያለነው። ስለዚህ ህዝቡ ተገናኝቶ ሰላሙን መመስረት ከቻለ መንግሥት ደግሞ ይከተላል ማለት ነው።”

”እንኳን ለመታረቅ ለመዋጋትም ከዚህ በፊት ውክልና አልሰጠንም። ስንዋጋም ሃገር የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትር ተዋጉ ሲል ተዋጋን እንጂ በውክልና አልተዋጋንም። የትግራይን ህዝብ ሳናካትት ምንም አይነት ለውጥም ሆነ እድገት ማሳካት አንችልም፤ አንፈልግምም።”

“ከትግራይ ህዝብ ውጪ ኢትዮጵያን የመቀየር ሃሳብ የለንም። ህዝቡ ያሳዝነናል፤ ህዝቡ ይቆረቁረናል። የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ጉዳይ ግድ አይሰጠውም ማለት አንችልም ምክንያቱም በባድመ ጦርነት ከማንም በላይ የሞቱት የኦሮሚያ ልጆች ናቸው።”

የሰላሙ ጉዳይ ለህዝባችን ስለሚጠቅም፣ የኤርትራ ህዝብ የሰላም ህዝብ ስለሆነ፣ የትግራይ ህዝብ ደግሞ የሚጠቀመው ከዚህ ሰላም ስለሆነ ሌላውን ትተን አንድ ሆነን እንስራ የሚለውን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጉረ ልውጦች እነማን ናቸው?

“ፀጉረ ልውጦች የተወሰኑ የአንድ ብሄር ተወላጆች ናቸው ብሎ ማሰብ በመሰረቱ የተሳሳተ ነው” በማለት የጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትግራይ ህዝብ ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ውስጥ ፀጉረ ልውጥ ሊሆን አይችልም።” ብለዋል።

“ኦሮሚያ ውስጥ ትግሬም ይሁን አማራ፤ ወላይታም ይሁን ጉራጌ፤ ህዝቡ ማንንም አቅፎ ለማኖር ፈቃደኛ ነው። እንደውም እኔና የወከልኩት ኦህዴድ ብዙ ችግር አለብን። የኦሮሞ ህዝብ ግን አቃፊ ነው። በእኛ መነጽር፤ በእኛ ልክ ህዝቡን አትለኩት። ህዝቡ እንደእኛ አይደለም፤ ህዝቡ ከእኛ የላቀ ብስለት ያለው ነው።”

“ፀጉረ ልውጥ ያልኩት በፍጹም አንድን ቡድን በሚገልጽ መልኩ ሳይሆን፤ የሚሰማሩ ሃይሎች ስለነበሩ መረጃው ስላለኝ ነው እንጂ የሆነ ቡድን ፀጉረ ልውጥ ሌላኛው ደግሞ ንጹህ ለማለት አይደለም። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ውጥረት ማንኛውም ነገር ለፖለቲካዊ ጥቅም ሊውል ይችላል።”

ባለፉት 27 ዓመታት የተሰራው ጥፋት ወይስ ልማት?

”ያለፉት 27 ዓመታ ብዙ ቆሻሻ ነገር የተሰራበት ዘመን ነው። ልማት ማለት አስፓልት፤ ልማት ማለት ኮንዶሚኒየም የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። መሰረተ ልማት ያለ ውስጣዊ ሥርዓት ምንም ጥቅም የለውም። ምክንያቱም እርስ በእርሱ የማይነጋገር ህዝብ፤ እርስ በእርሱ የማይግባባ ህዝብ ፈጥረን ስናበቃ አስፓልት ሰርተንልሃል የምንል ከሆነ ተገቢ አይደለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ለተገኘው ልማት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተገኘው ሰላም ባለቤቱ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለጠፋው ጥፋት ግን ተጠያቂው መንግሥት ነው። ጥሩ ነገር ሲሰራ ሃላፊነት የምንወስድ፤ ጥፋት ሲጠፋ ደግሞ የምንሸሽ አክራሪዎች አይደለንም እኛ፤ መንግሥት ነን። እስከ ዛሬ ለጠፉ ጥፋቶች በሙሉ ኢህአዴግ እንደ መንግሥት ሃላፊነቱን ወስዶ ህዝቡንም ይቅርታ ጠይቋል።

ይሄ ሁሉ ግን በይቅርታ ብቻ የሚያልፍ አይደለም። ባለፉት 27 ዓመታት ለገረፍናችሁ፣ ላባረርናችሁ፣ ላስቸገርናችሁ ሰዎች እኔ እንደ ኢህአዴግ ከልብ ይቅርታ እጠይቃችኋለው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.