NEWS: የኢትዮጵያና የኤርትራ አየር መንገዶች በሽርክና ሊሰሩ ነው

የአሰብ ወደብ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤርትራ አየር መንገድ ላይ ድርሻ እንደሚኖረው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም የኢትዮጵያና ኤርትራ መሪዎች አሥመራ ላይ የደረሱት የሠላምና የወዳጅነት የጋራ ስምምነት ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ እንዳሉት ሁለቱ መሪዎች ከተፈራረሟቸው ስምምነቶች መካከል በትራንስፖርት፣ በንግድ እና በኮምዩኒኬሽን ዘርፎች ላይ የደረሷቸውን ስምምነቶች በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

• ከአዲስ አበባ ወደ አስመራ የሚወስዱ አውራ ጎዳናዎች

• የኤርትራና የኢትዮጵያ መጪው ፈተና

ከሁለት አስርታት በኋላ የመጀመሪያውን በረራ ወደ አሥመራ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድም በኤርትራ አየር መንገድ ላይ ሃያ በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው የተገለፀ ሲሆን፤ አየር መንገዱ ረቡዕ እለት 465 መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዛል።

የአሰብ ወደብን በተመለከተም ሁለቱ መሪዎች ወደቡ በአፋጣኝ አገልግሎት እንዲጀምር በተስማሙት መሰረት በኢትዮጵያ በኩል የተለያዩ አካላት ያሉበት ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ አስፈላጊ ሥራዎችን እየተሰሩ መሆኑን አቶ መለስ አመልክተዋል።

ከወደቡ ቁሳቁሶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ የሚያስችሉ መንገዶች ጥገና በሁለቱም ሃገራት በኩል እየተከናወነ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ጨምረው ተናግረዋል።

በቴሌኮምዩኒኬሽን በኩልም የስልክ አገልግሎት ከተጀመረ ቀናት መቆጠራቸውን አመልክተው በሁለቱ ሃገራት ያሉ ሰዎች ግንኙነት መቀጠሉም ተገልጿል።

• የኢትዮጵያና ኤርትራን የአብሮነት እርምጃ ምን ይፈትነዋል?

• ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢትዯጵያና የኤርትራ ሕዝቦች አንድ ናቸው አሉ

የኤርትራ ኤምባሲ አዲስ አበባ ላይ መከፈቱን ተከትሎ ኢትዮጵያም አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመክፈት አስፈላጊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ ጉዞ ላይ ባለሥልጣናት፣ የንግድ ሰዎችና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለበርካታ ዓመታት ተለያይተው የቆዩ ሰዎች በነገው የመጀመሪያ በረራ ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቲኬት ቢሮውን አሥመራ ውስጥ የከፈተ ሲሆን በቀን ሁለት በረራዎችን ለማድረግ ዕቅድ እንዳለውም ታውቋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.