NEWS: የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ

በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ።

በፕሬዚዳንቱ ለተመራው ልዑክም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው አሸኛኘት አድርገዋል።

ዛሬ ማለዳ ላይ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በብሄራዊ ቤተመንግስት አሸኛኘት የተደረገላቸው ሲሆን፥ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

በመቀጠለም ለሁለት አስርት ዓመታት ለሚደርስ ጊዜ ተዘግቶ የነበረው የኤርትራ ኤምባሲንም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በመሆን ዳግም ከፍተዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሃዋሳ ጉብኝት አድርገዋል።

ከሽኝቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሰጡት መግለጫ፥ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ወደ አዲስ አበባ መግባት ተከትሎ የከተማው ህዝብ የሞቀና ደማቅ ፍቅር የተሞላበት አቀባበል በማድረጉ ለመዲናዋ እና አካባቢዋ ነዋሪዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሐዋሳ በነበራቸው ቆይታም የሐዋሳ ከተማ ህዝብ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስና ለልዑካን ቡድናቸው በቄጤላ ባህል የታጀበ ደማቅ አቀባበል ማድረጉን አንስተው ለተደረገላቸው የሞቀ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በሚሌኒየም አዳራሽ በነበረው ቆይታም “የጥላቻ፣ የቂም እና የክፋት ግንብ የፈረሰበት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ሊገነባ የታሰበው ድልድይ ዳግም ሊናድ እንዳይችል ሆኖ እንዲገነባ የተደረገበት ምሽት ነበር” ብለዋል፡፡

“ከኤርትራ ልዑክ ጋር በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፀጥታ ዘርፍ አብረን በመስራት የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ህይወት ማሻሻል እንደሚጠበቅብን ተስማምተናል” ነው ያሉት።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረው እርቅ አብዛኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት ብሩህ ተስፋ ከፊታችን እንዳለ ያሳየ መሆኑን በመግለፅ፥ ለመልማት እና ለመትጋት እስከተወሰነ ድረሰም ሰፋፊ እድሎች ከቅርብም ከሩቅም እየመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

“ይህንን ሰላም ተከትሎም በርካታ ሀገራት የልማት ስራዎቻችንን ለማገዝ እና ለመደገፍ ከጎናችን ለመቆም እያሳዩት ያለው ተነሳሽነት ተስፋ ሰጪም” ነው ብለዋል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.