“ኢትዮጵያና ኤርትራን የሚለያቸው የለም” ኢሳያስ አፈወርቂ

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው አዲስ የሰላምና የወዳጅነት ምዕራፍ ማብሰሪያ ሥነ-ሥርዓት በሚሊኒየም አዳራሽ ትላንት ተካሂዷል። የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዝግጅቱን ታድመውታል።

በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ኢትዮጵያና ኤርትራን የሚለያቸው የለም” ሲሉ ተደምጠዋል፤ “የሁለቱ ሃገራት ሰላም ጠቃሚነቱ ለቀጣናው ጭምርም ነው” ሲሉም አክለዋል።

“ለውጡን ማንም ሊያቆመው አይችልም፤ ኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ዐብይ አላት፤ አንዱ ቢያልፍ አንዱ ይተካል” የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መልዕክት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተው የነበሩ ታዳምያንን ‘ይደግምልን’ ያስባለ መስመርም ተናገርረዋል፤ “እኔ ኢሳያስ አንድ ላይ ስንሆን አሰብን እንጋራለን” በማለት።

“የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰላም ለቤተሰብና ለጎረቤት ትምህርት ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደ ኢትዮጵያ ሊተያይ ይገባል” ሲሉ አስረግጠዋል።

“ነጻነት፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍቅር ብርሃን እንጂ ጨለማ አያመነጨውም፤ ጨለማም ከእነዚህ ጋር ስምምነት የለውም። ስለሆነም የተገኘውን ሰላም፣ ዴሞከራሲና ነጻነት መጠበቅ ያሰፈልጋል” ሲሉ በጭብጨባ የታጀበ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

"ኢትዮጵያና ኤርትራን የሚለያቸው የለም" ኢሳያስ አፈወርቂImage copyrightETV

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው “የኤርትራን ህዝብ ሰላምታና ፍቅር ለኢትዮጵያ ህዝብ ይዤ መጥቻለሁ” ሲሉ ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት።

“በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላምና የሚታሰበውን የጋራ ልማት ማንም ኃይል አንዲፈታተነው አንፈቅድም” ሲሉም አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

“ጥላቻን አስወግደን ልማትና ብልፅግና ለማምጣት በሁሉም መስኮች ተባብረን ወደፊት ለመራመድ ቆርጠን ተነስተናል” የኢሳያስ ድምፅ ነበር።

ፕሬዝደንቱ በአማርኛ መልዕክታቸውን ባስተላለፉበት ወቅት በርካቶች በጭብጨባ ሲያጅቧቸውም ተስተውለዋል።

• የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባ ገቡ

• ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የኢትዯጵያና የኤርትራ ሕዝቦች አንድ ናቸው አሉ

• ስለ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምን ያህል ያውቃሉ?

ይህን ተከትሎም በኬንያ የኤርትራ አምባሳደር የሆኑት በየነ ርዕሶም “ኢሳያስ እንባ እየተናነቃቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ በአማርኛ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። አኔ ኢሳያስን ለ40 ዓመታት አውቃቸዋለሁ፤ በአማርኛ ሲያወሩ ሰምቼ ግን አላውቅም” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

በርካታ ሺዎች ታድመውበታል በተባለው ዝግጅት ላይ ታዋቂ ድምፃዊያን ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን ተወዳጁ ድምፃዊ ማሃሙደ አሕመድ ‘ሰላም’ በተሰኘ ሥራው ታዳሚውን አስፈንጥዟል።

ኢትዮያዊያንና ኤርትራውያን ዘርና ሃይማኖት ሳይለያቸው የታደሙበት ይህ ‘የሰላም ማብሰሪያ’ ዝግጅት የተሳካ እንደነበርም በሥፍራው የነበረው የቢቢሲ ጋዜጠኞች ቡድን ታዝቧል።

ለቢቢሲ ድምፃቸውን የሰጡ ታድምያን የመሰል ዝግጅት ተሳታፊ መሆናቸው ውስጣዊ ፍስሃ እንዳደላቸው አልሸሸጉም።

በፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው የኤርትራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ እያካሄደ ያለውን የሦስት ቀናት ጉብኝትን አጠናቆ ዛሬ ወደ ኤርትራ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.