የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች ከዚህ በኃላ ሁለት ህዝቦች ናቸው ብሎ የሚያስብ እውነታውን ያልተረዳ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተናገሩ፡፡

በኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተመራው የልዑካን ቡድን በፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ደማቅ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ የምሳ ግብዣም ተደርጎለታል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዕለቱ ታሪካዊ ቀን መሆኑን እና በተደረገላቸው መንግስታዊና ህዝባዊ አቀባባል መደሰታቸውን  ተናግረዋል፡፡

“ከዚህ በኋላም የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ሁለት ሕዝቦች ናቸው ብሎ የሚያስብ እውነታውን ያልተረዳ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩልም በአርቲስት ለማ ጉያ የተሰራ የራሳቸው ምስል ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ  ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በበኩላቸው  ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል ለማድረግ የወጣውን ህዝብ አመስግነዋል፡፡

“24 ሰአት ብንሰራለት፣ ደማችንን ብናፈስለት የሚያንሰው ህዝብ ፤ ምንም ሳናደርግለት እንደዚህ ለወደደን፣ ፍቅሩን ለገለፀልን… ህዝብ ምስጋና ይገባዋል፡፡”

በአቀባባልና እና በምሳ ግብዣ ስነ ስርዓቱ ላይ የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጨምሮ  ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የሐይማኖት አባቶች፣የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከቀትር በኋላ ወደ ሀዋሳ በማቅናት  የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በከተማ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ለኤርትራ ልዑካን ቡድን አቀባባል ለማድርግ የወጡ የአዲስ አበባና አጎራብች ከተማ ነዋሪዎች ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራን ሰንደቅዓማዎች ይዞ ከመውጣት ጀምሮ የተለያዩ መፈክሮችንና ዝማሪዎችን በጭፈራ ጭምር ሲገልፁ ተስተውሏል፡፡

ምንጭ: ኢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.