NEWS: Emirates Plans To Start Vertical Farm in Dubai | ከመሬት በላይ የእርሻ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ሰፊ ፕሮጀከት በዱባይ ይፋ ሆኗል

ከመሬት በላይ የእርሻ ምርቶችን ማምረት የሚያስችል ሰፊ ፕሮጀከት በዱባይ ይፋ መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ ከመሬት በላይ የግብርና ምርቶችን በማምረት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቁ ሲሆን፥ ዱባይ በዘርፉ ውጤቶች እረሷን እንድትችል ያግዛል ተብሏል።

የተባበሩት አረብ ኢሚሬት አየር መንገድ ለዚሁ ፕሮጀከት 40 ሚሊየን ዶላር በጀት እንደያዘም ታውቋል።

ፕሮጀክቱ የእርሻ ምርቶችን በማምረት ለአየር መንገዱ ግባዓት ለማቅረብ ከማስቻሉም በላይ ለዘርፉ ትራንስፖርት፣ ምግብና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶች ከሚውለው ሃይል የሚወጣውን የካርበን ዳይ ኦክሳይድ ጋዝ ልቀት ለማመጣጠን ያስችላል ተብሏል። ፕሮጀክቱ የፊታችን ህዳር በዱባይ አል ማከቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ አካባቢ ግንባታው የሚጀመር ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ አንድ አመት ያህል ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል ነው በዘገባው የተመላከተው።

12 ሺህ 77ነጥብ4 ስኮየር ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው ይህ ፕሮጀከት 364ነጥብ2 ሄክታር መሬት ላይ የሚመረት ምርትን ያህል የእርሻ ውጤቶችን ለማምረት እንደሚያስችል ነው የተገለጸው።

ፕሮጀክቱ በየትኛውም የአየር ንብረት አካባቢ በጥቂት ውሃና ውስን ቦታ በርካታ ምርትን ለማግኘት ያስችላል ተብሏል።

በዚሁ ፕሮጀከት መሬት ላይ 161ነጥብ9 ሄክታር ቦታ የሚፈጅን የእርሻ ልማት በ 0ነጥብ4 ሄክታር ቦታ ላይ ለማምረትም እንደሚቻል ነው የተገለጸው።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.