NEWS: “ዛሬ ትግርኛ የለ፣ አማርኛ የለ! ቋንቋው ጠፍቶብኛል” ዐብይ አሕመድ

ሁለቱ መሪዎች በትናንቱ የእራት ግብዣ ላይ አብሮ ለመሥራት መስማማታቸውን፣ አዲስ የወዳጅነት ምዕራፍ መከፈቱን የሚያበስሩ ንግግሮችን አሰምተዋል። ታዳሚውም በተደጋጋሚ የሁለቱን መሪዎች ንግግሮችን በጭብጨባ ሲያጅብ ነበር።

የፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ንግግር በአጭሩ

“ዛሬ በአስመራ ሕዝቡ ወጥቶ ያሳየው ትዕይንት ሌላ ተጨማሪ ንግግር አያስፈልገውም። የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ብቻ አይደለም፤ ከልቡ የቆየውን እምቅ ፍላጎት ነው በይፋ የገለፀው። በዚህ አጋጣሚ ሁለቱንም ሕዝቦች እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። የዚችን ሀገር እውነተኛ ስሜት ምን እንደሚመስል አይታችሁታል። ዶክተር ዐብይ የወሰደው ምርጫ ቀላል ምርጫ አይደለም። ለ25 ዓመታት ያጠፋነው ግዜ፣ ያከሰርነው ዕድል በምንም መለኪያ መስፈር የሚቻል አይደለም። አሁን ግን አልከሰርንም። ከዚህ በኋላ ባለው ጉዟችን ከዶክተር ዐብይ ጋር አብረን ነን። የሚገጥመንን ፈተናም ሆነ መልካም ዕድል አብረን እንወጣዋለን።”

• የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አዲስ ምዕራፍ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ንግግር ባጭሩ

“ዛሬ ትግርኛ የለ፥ አማርኛ የለ! ቋንቋው ጠፍቶብኛል። ደስታዬን ግን ፊቴ ላይ ዕዩት።…ክቡር ኢሳያስ፣ (በኤርትራኛ ወዲ አፎም)፣ለኤርትራ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ፣ አለን። ብዙ ሕዝብ ካለቀ በኋላም ቢሆን አሁን የጀመርነው ጉዞ አልረፈደም። እናንተ ኤርትራዊያን ሠላም ሀዋርያት የሆናችሁ፤ ከሠላም ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ….። ሠላም አይደለም ለሠው ለሠማይ አእዋፍ እንኳን አስፈላጊ ነው።

አሁን ሁላችሁም ኢትዮጵያዊ ናችሁ። የኤርትራ ጳጳሳትና ሸሆች የኢትዮጵያም ናችሁ። ለልጆቻችሁ ሠላምና ፍቅር መፀለይ አለባችሁ።…ልጆቻችን እኛ ያሠርነውን ገመድ ፣ ያጠርነውን አጥር….እንዲያፈርሱ እናድርግ…።

የኤርትራ ሕዝብ ሆይ! የሰለጠንክና ሥራ ወዳጅ ነህ ። ግን ሰላም ከሌለ ፍሬያማ አትሆንም…። ለናንተ ሠላም ይገባችኋል። ስለ ውጊያ መስማት ይበቃናል። እኛ ሰላም ከሆንን ምሥራቅ አፍሪካም ሰላም ትሆናለች ።…በሌላ አገር ያሉ የሁለታችንም ዜጎች እንደ ዕቃ ሣይሆን በክብር እንቀበላቸዋለን ። በውቅያኖስ ሣይሆን በክብር እንልካቸዋለን። አስመራ ብዙ አማርኛ የሚችሉ ሕዝቦች ስላሉ በአማርኛም ልናገር…ዛሬ…”

• የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ?

ስምምነቶች

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ትናንት ምሽት የኤርትራው ፕሬዝደንት የእራት ግብዣ ባደረጉላቸው ወቅት የተናገሩት፥ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ለተደረገላቸው አቀባበል እና ለተሰጣቸው ፍቅር ፕሬዝደንት ኢሳያስን እና የኤርትራን ሕዝብን ያመሰገኑ ሲሆን፤ በፍጥነት በመሥራት የሁለቱን አገራት ሕዝብ እንክሳለን ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር በነበራቸው ውይይት ሦስት ዋና ዋና የሚባሉ ስምምነቶችን ፈጽመዋል።

1ኛ-በሁለቱም አገራት ኤምባሲዎች እንዲከፈቱ

2ኛ- አየር መንገዶች ሥራ እንዲጀምሩ

3ኛ- ወደቦች ሥራ እንዲጀምሩ መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement