የህዝብ ተወካዮች ምክር የ123 ዳኞችን ጨምሮ የተለያዩ ሹመቶችን አፀደቀ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር በዛሬው እለት ባካሄደው 6ኛ ልዩ ስብሰባ የተለያዩ ሹመቶችን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ የመጀመሪያና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ኮሚሽነርን እንዲሁም የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዋናና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንባ ጠባቂዎች ሹመትን ነው ያፀደቀው።

በዚህም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 41 ወንዶች እና 8 ሴቶች በድምሩ 49 ዳኞችን፤ ለፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ደግሞ 58 ወንዶች እና 16 ሴቶች ድምር 74 ዳኞች፤ በአጠቃላይ የ123 ዳኞችን ሹመት በአንድ ተቃውሞና በሁለት ድምጽ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ኮሚሽነር የወይዘሮ መሰረት ማሞን ሹመት በአንድ ተቃውሞና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የዋናና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት እንባ ጠባቂዎችን ሹመት በዛሬው እለት አጽድቋል።

በዚህም ደክተር እንዳለ ሀይሌን ለዋና እንባ ጠባቂነት፣ አቶ አህመድ ሁሴን ለሰመራ እንባ ጠባቂ ቅርንጫፍ፣ አቶ ጀምስ ዴንግ ለጋምቤላ ቅርንጫፍ፣ አቶ ፍቃዱ ታደሰ ደግሞ ለአሶሳ እንባ ጠባቂ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለዕጩነት ቀርበው ሹመታቸው በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

በተመሳሳይ አጀንዳ ምክር ቤቱ ለኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን የተጓደሉ የስራ አመራር ቦርድ አባለትን ለማሟላት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳየዮች ሀላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴን የቦርድ ሰብሳቢ ሾሟል።

በተጨማሪም ወይዘሮ ሃሊማ ባድገባ፣ ክቡር አቶ ፍስሃ ይታገሱ እና ዶክተር መረራ ጉዲናን የቦርድ አባል አድርጎ ሹመቱን በአራት ተቃውሞና በሁለት ድምጽ ተዓቅቦ አጽድቋል።

በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን የተቀቡለተም ህዝብና መንግስት የጣሉባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በቅንነት፣ በታማኝነት እና በታታሪነት ለመወጣት ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.