የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ትርፍ?

ኢትዮጵያ ለኤርትራ ላደረገችው የሰላም ጥሪ ኤርትራ ልዑካን ወደ አዲስ አበባ እልካለሁ ማለቷን ተከትሎ የሁለቱ አገራት ቀጣይ ግንኙነትን በሚመለከት የተለያዩ ሃሳቦች እየተሰነዘሩ ነው።

የሁለቱ ሃገራት ህዝቦች ባህል፣ቋንቋንና በርካታ እሴቶችን የሚጋሩና በብዙ መልኩ የሚተሳሰሩ ናቸው። አገራቱ ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት ጠንካራ ግንኙነት እንደነበራቸው የሚታወስ ነው።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሁለቱ አገራት መካከል በትክክልም ሰላም ማውረድ ከተፈለገ ስምምነቱ በመሪዎች ደረጃ የሚደረግ ፖለቲካዊ ስምምነት ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ከግንዛቤ ያስገባ መሆን እንዳለበት እየተገለፀ ነው።

ሁለቱ አገራት ተሳክቶላቸው ግንኙነታቸውን ወደ ቀድሞ መመለስ ከቻሉ አገራቱ በተለይም ከኢኮኖሚ አንፃር ከግንኙነቱ ምን ያተርፋሉ?ህዝቡስ ምን ያገኛል? እንዲሁም ግንኙነቱ ዳግም እንዳይደናቀፍ ምን ማድረግ ይቻላል ?የሚሉና መሰል ጥያቄዎች ይነሳሉ።

መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉት የአለም አቀፍ ግንኙነትና ኢኮኖሚ ትብብር ኤክስፐርት አቶ አብዱራህማን ሰኢድ የሁለቱ አገራት መልካም ግንኙነት መፍጠር ለሁለቱም ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው ይላሉ።

ከአንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት ኢትዮጵያ ለኤርትራ ሰፊ ገበያ መሆን መቻሏ፣ኤርትራ ወርቅን የመሰሉ ማእድናት ያሉባት መሆኗ፣ኤርትራ በምግብ ምርት ራሷን የቻለች አለመሆኗና ኢትዮጵያ ይህን ክፍተት መሙላት፤እንዲሁም ኢትዮጵያ የኤርትራ ወደቦችን መጠቀም መቻሏና ይህ ደግሞ ለኤርትራ ትልቅ ጥቅም እንደሚሆን በመጠቃቀስ ነጥባቸውን ያስረዳሉ።

የግንኙነቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ግን በሁለቱም አገራት በኩል መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ተቋማዊ ስርአት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

በአሁኑ ወቅት እየተደረጉ ባሉ መሻሻሎች ምክንያት በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ምንም ችግር ባይኖርም በኤርትራ በኩል ግን ብዙ ስራ እንደሚቀር ያስረዳሉ።

“በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት መጠበቅ እንዲሁም የፖለቲካ ነፃነት አለ።በተቃራኒው በኤርትራ የአንድ ሰው አገዛዝ ስርአት ነው ያለው”የሚሉት አቶ አብዱራህማን በአገራቱ መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ዲሞክራሲያዊ ስርአት እስካልተገነባ ድረስ ለአገራቱ ሰላም ኢኮኖሚያዊ ግንም ዋስትና የሚሆን ነገር እንደማይኖር ይገልፃሉ።

በጦርነቱ ዋዜማ የሁለቱ አገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙት ምን ይመስል አንደነበር የሚያስታውሱት የቀድሞ አየር ሃይል አዛዥ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖትም የአቶ አብዱራህማንን ሃሳብ ይጋራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ቀድሞ በሁለቱ አገራት መካከል መልካም ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት ይኖራል የሚል እምነት ነበር።ነገር ግን በወቅቱ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ባልተገባ መልኩ ሊጠቀም መፈለጉ ችግር ፈጥሯል።

“በተለይም ኤርትራ የራሷን ገንዘብ ናቅፋን ማተሟን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሁሉም ግብይቶች በዶላር እንዲሆኑ መወሰኗን ኤርትራ እንደ ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅፋት በመቁጠር ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ተነሳች”ይላሉ።

ያ የኢኮኖሚ ግንነኙነት እንከንም በድንበር ስም ለሁለቱ አገራት ጦርነት ውስጥ መግባት ምክንያት እንደሆነ ይገልፃሉ።

አቶ አብዱራህማንም በሁለቱ አገራት ዋስትና የሚሰጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እስከሌለ ድረስ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶቹ መቀጠል ቢችሉ እንኳን ሃይል ላላቸው ቡድኖች እንጂ ለህዝቡ ወርዶ ጠብ የሚል ነገር እንደማይኖር ያስረዳሉ።

ከዚህ ሲያልፍም ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱ ዳግም የግጭት ምክንያት የመሆን ሰፊ እድል እንደሚኖረው አቶ አብዱራህማን ያሳስባሉ።

ነገር ግን ለኢኮኖሚ ግንኙነቱ የሚሉት አይነት ዋስትና የሚሰጥ ስርአት መዘርጋት ከተቻለ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ሰፊ ማህበራዊና ባህላዊ እሴት የሚጋሩት እንደ ጅቡቲና ሶማሊያ ያሉ አገራትን ጨምሮ ጠንካራ አካባቢያዊ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መዘርጋት እንደሚቻል አቶ አብዱራህማን ትልቅ ተስፋ አላቸው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.