“ወትሮም ቢሆንም የትጥቅ ትግል ፍላጎት የለንም” ግንቦት 7

ከጥቂት ቀናት በፊት የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ “የጥትቅ ትግል ያለፈበት ስልት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትሩ በጎረቤት ሃገራት ሆነው የትጥቅ ትግል አማራጭ አድረገው የሚገኙ ቡድኖች ወደ አገር ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅረበው ነበር።

ይህንን የጠቅላይ ሚንስትሩን ጥሪ ተከትሎም አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ”የስለጠነ ፖለቲካ” የምንመርጠው፣ የምናውቀውና የምንመኘው የትግል ስልት ነው” ብሎ ባወጣው መግለጫ የጠቅላይ ሚንስትሩን የሰላም ጥሪ መቀበሉን ገልጿል።

ግንቦት 7 ትናንት ባወጣው ልዩ መግለጫ “የትጥቅ ትግል እንዲሁም ግንባሩ ጥይት የተኮሰው ለመከላከል እንጂ አንደ ህወሃት ስልጣን ለመያዝ”ተልሞ እንዳልሆነ አስምሯል።

ዶ/ር ታደሰ ብሩ የአርበኞች ግንቦት 7 የሥራ አስፈጻሚ አባል እና የህዝባዊ እምቢተኝነት ክንፍ ኃላፊ “ድሮም ቢሆን የትጥቅ ትግል ፍላጎት አልነበረንም፤ በመሣሪያ ትግል የፖለቲካ ግብ የማሳካት ፍላጎትም ዓላማም ኖሮን አያውቅም። ይልቁንስ ከጉልበተኛ መንግሥት ራሳችንን እንከላከላለን የሚል ነበር እንጂ መሣሪያን ተጠቅመን ሥልጣን እንያዘለን የሚል አቋም ኖሮን አያውቅም” ይላሉ።

በቅርቡ ከእሥር የተለቀቁት የግንቦት 7 መሥራች አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ‘ግንቦት 7 አንድም ጥይት ተኩሶ አያውቅም’ ማለታቸው አይዘነጋም።

ይህንን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ዶ/ር ታደሰ “ምናልባት ራሳችንን ለመካለከል ጥይተ ተኩሰን እናውቅ ይሆናል እንጂ ዓለማችንን ለማሳካት ብለን አድርገነው አናውቅም” ይላሉ።

“ዋነኛ ስትራቴጂያችን ሕዝባዊ እንቢተኝነት ነው» የሚሉት ኃላፊው “አፋኝ የሆነና ለሰላማዊ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ላይ ጥይት የሚተኩስ መንግሥት ባለ ጊዜ ራሳቸውን መካለከል የሚችሉ ቡድኖች ያስፈልጋሉ፤ ለዚህ ደግሞ መደራጀት ያስፈልጋል፤ መሰልጠንም ግድ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

አርበኞች ግንቦት 7 ይህንን መግለጫ ያወጣው መሽጎባት የምትገኘው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ለመፍጠር መወሰኗን ተከትሎ ነው የሚሉ ትንታኔዎች መሰማት ጀምረዋል።

ዶ/ር ታደሰ ግን “ይህን ውሃ አያነሳም” ይላሉ። “እንደውም እኛ ስምምነቱን በበጎ ጎኑ ነው የምንመለከተው። በዶ/ር አብይ በምትደዳረው ኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሚኖረው መቀራረብ ከሁለቱ ሃገራት አልፎ ለቀጣናው መረጋጋት ጠቀሜታ አለው ብለን እናምናለን” ይላሉ።

ወደ ሃገር ቤት የመመለስ ነገር. . .

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በውጭ ሃገራት የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሃገር ቤት ተመልሰው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ማቅረባቸው የሚዘነጋ አይደለም።

ይህንነወ ተከትሎም በተለይም ለኦሮሞ ነፃነት የሚታገሉ አንዳንድ ፓርቲዎች ልዑካንን መላክ መጀመራቸውም ተዘግቧል።

“እስካሁን የማውቀው ይፋ የሆነ ነገር ባይኖርም እርምጃውን በቀና መልኩ ነው የምናየው፤ በዘመናዊ ፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጎታችንም ፅኑ ነው። ቢሆንም አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ ዘላቂ መሆኑን ማረጋገጥ አንፈልጋለን። ለምሳሌ የፀረ-ሽብር ሕጉና ሌሎች አፋኝ ሕግጋት መነሳት አለባቸው። ግንቦት 7፣ ኦነግና አብነግና ሌሎች ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ላይ የተፈረጀው ፍረጃም መነሳት አለበት በለን እናምናለን” ይላሉ።

ግንቦት 7 በመግለጫው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራትን እንደሚያደንቁ አስታውቋል።

“ምንም እንኳ ነገሮች በአንድ ጀምበር ይከናወናሉ ብለን ባናምንም ወደፊት የተሻለ ተቋማዊ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ አለን”ይላሉ ዶ/ር ታደሰ፤ ወደ ሃገር ቤት የመመለሳቸው ጉዳይ በመፃኢ ኹነቶች ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ በማስረገጥ።

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ወደቀደመ ሥራቸው መመለሳቸውን ያሳወቁት ዶ/ር ታደሰ «መግለጫውን ያወጣነው እሳቸው ስለተመሱ ግን አይደለም» ይላሉ። «አሁን ይፋ ያደረግነው አቋም በፊት የነበረ ነው፤ አሁንም ደግሜ የምለው ሕዝባዊ እንቢተኝነታችንን ለመደገፍ እና ራሳችንን ለመከላከል ያደረግነው እንጂ የትጥቅ ትግል ፍላጎት የለንም» ሲሉ ያስረግጣሉ።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.