ኢትዮጵያና ኤርትራ የት ድረስ አብረው ይራመዳሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ሲረከቡ ፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማውረድ እንደሚፈልጉ አስታውቀው ነበር።

በወቅቱ ከኤርትራ በኩል የተሰጠው ምላሽ ኢትዮጵያ ሰላም ማውረድ ከፈለገች የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ ቀዳሚው እርምጃ ነው የሚል ነበር።

ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ እንደምታደርግ ስታስታውቅ በአገር ውስጥ ውሳኔውን የመቃወም ድምፆች ተሰምተው ነበር። በኤርትራ በኩል ግን ምንም የተባለ ነበር አልነበረም።

ዛሬ ግን ዝምታው ተሰብሮ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ አዲስ አበባ ልኡካን እንደሚልኩ አስታውቀዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆነው መኃሪ ዮሃንስ ዘላቂ ሰላምን ያመጣል የሚለው ጉዳይ ዛሬ ላይ የሚመለስ ባይሆንም እርምጃው ግን በራሱ ትልቅ ነው ይላል።

እርምጃው ትልቅ ነው የሚለው የእስከዛሬውን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከግምት በማስገባት ነው።

የሁለቱ አገራት መንግስታት ላለፉት ሃያ ዓመታት ደረቅ አቋም ይዘው የኢትዮጵያ መንግስት የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በመርህ ደረጃ ተቀብለነዋል ነገር ግን ትግበራው ውይይት ይፈልጋል ፤ የኤርትራ መንግስት ደግሞ ውሳኔው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፈፀም አለበት ሲሉ ከመቆየታቸው አንፃር እርምጃው የፖሊሲ ለውጥ ነውም ይላል።

ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ንግግር እንደተረዳው ዋናው ችግር የነበረው በኤርትራው ገዥ ፓርቲና በህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ(ህወሃት) መካከል እንደነበርና አሁን ግን በኢትዮጵያ የአመራር ለውጥ መምጣቱ ፕሬዝዳንቱን ለውሳኔው አብቅቷቸዋል።

ይህን “በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል መናበብ ያለ ይመስላል”በማለት ይገልፀዋል መኃሪ።

የኤርትራ መንግስት ልኡክ ለመላክ በመወሰን የወሰደው እርምጃ ምን ያህል ጉልህ ነው የሚለው የሚመዘነው ልኡካኑ መጥተው በሚያደርጉት ውይይት እንደሆነ መኃሪ ያስረዳል።

ልኡካኑ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር የሁለቱ አገራት መሪዎችን ለማገናኘት ነገሮችን ለማመቻቸት ወይስ በድንበር ጉዳዩ ላይ ለመነጋገር የሚለውን ማወቅ እርምጃውን ለመመዘን ወሳኝ እንደሆነ ያምናል።

“እርምጃው ዘላቂ ሰላምን ያመጣል አያመጣም የሚለው ጊዜው ደርሶ የውይይቱን ርእሰ ጉዳዮች ማወቅ ይጠይቃል”ብሏል።

ከሁለት አስርታት በላይ በአገራቱ መካከል የዘለቀውን ዝምታ ለሰበሩት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጡ የሚናገሩት ኤርትራዊው የህግ ባለሙያና ግጭት አፈታት ኤክስፐርት አቶ ኤልያስ ሃብተስላሴ የኤርትራ መንግስት ወደዚህ ነገር የገባው ተገዶ ነው ይላሉ።

ቢሆንም ግን ለንግግር በር መክፈቱ ትልቅ ግምት የሚሰጠው እንደሆነ ያምናሉ።

እርምጃው ምን ድረስ የሚዘልቅ ነው የሚለውን ለማወቅ ጊዜ እንደሚጠይቅ “ምን ያህል ነው በሩን ክፍት ያደረገው የሚው በጊዜው የሚታይ ነው”በማለት በመኃሪ ሃሳብ ይስማማሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የኤርትራ መንግስት ወጣቱን በብሄራዊ ግዳጅ ሲያስገድድና ህዝቡ ላይ የተለያዩ ተፅእኖዎችን ሲያሳደር ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ላለማድረግ እንቢተኛ ሆናለች በሚል ነበር።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ባደረጋቸው ውሳኔዎች ምክንያት የኤርትራ መንግስት በቀደመው አቋሙ እንዳይቀጥል ሆኗል የሚል እምነት አላቸው።

በሁለቱ አገራት ግጭት በደረሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት ግን ጅማሮውን ከዳር ማድረስና በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም ማስፈን ብዙ ስራ የሚጠይቅ እንደሚሆን አቶ ኤልያስ ይገልፃሉ።

እንደ እሳቸው አገላለፅ በሁለቱ አገራት መንግስታት ምክንያት ሞት፣አካል ጉዳት፣መፈናቀል በአጠቃላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ቀውሶች በሁለቱም ህዝቦች ላይ ደርሰዋል።በተለይም በሁለቱም በኩል ድንበር ላይ ያሉ ህዝቦች ይበልጥ ተጎድተዋል።

ስለዚህም በሁለቱ አገራት ሰላም የማስፈን ነገር በመሪዎች ስምምነት ብቻ የሚጠናቀቅ ጉዳይ እንዳልሆነ አቶ ኤልያስ ያስረዳሉ።

ይልቁንም የተጎጅዎች ካሳ ፣ሁለቱን ህዝብ የማገናኘትና ወደ ቀደመ ዝምድናው የመመለስ ጉዳይ ሊተኮርበት እንደሚገባ ያምናሉ።

ለዚህ ደግሞ ስምምነቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ገፅታ ሊኖረውና ሲቪል ማህበራትን ፣ የሃይማኖት ተቋማትንና በሁለቱም አገራት በኩል የሚመለከታቸውን እንዲሁም አህጉራዊና አለም አቀፍ አካላትን ሊያሳትፍ እንደሚገባ ያስረዳሉ።

ይህ ካልሆነ ግን አዎንታዊው ጅማሮ ግቡን አይመታም የሚል ስጋት አላቸው።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.