NEWS: PM Dr. Abiy Speech To The Parliament | ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በምክር ቤቱ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጡ

http://www.planetethiopia.com/videos/live-primeminister-abiy_4a27efbd9.html

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ዙሪያ እና ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በሃገሪቱ በተከሰቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ምክንያት፥ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

በዚህ ሳቢያም እድገቱ ወደ አንድ አሃዝ መውረዱን ጠቅሰዋል፤ ከግብርናው ጋር በተያያዘ በ2008 ዓ.ም በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተከሰተው ኤል ኒኖ የተስተዋለው የምርት መቀነስ በ2009 እና 2010 እያገገመ መምጣቱን ገልጸዋል።

አሁን ላይም ዘርፉን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ መስኖ ለማሸጋገር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በኢንዱስትሪው መስክ የማምረቻውን ዘርፍ ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዘርፉን በኢኮኖሚው መስክ ቀዳሚ ለማድረግ ከተያዘው እቅድ አንጻር ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ከወጪ ንግድ አፈጻጸም አንጻር በሰጡት ማብራሪያ ዘርፉ ለተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋና ምክንያት መሆኑን ጠቁመው፥ የወጪ ንግዱን ከማጠናከር ባለፈ ሌሎች የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ይደረጋሉ ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችእ ላይ ማሻሻየዎችን ማድረግና ህገ ወጥ ንግዱን በመቆጣጠር ዘርፉን ለማሻሻል ጥረት ይደረጋልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሁን ላይ ሃገሪቱ የተበደረችውን ብድር የመክፈል አቅም ማጣቷንም ነው በማብራሪያቸው ያነሱት።

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅም ለእዳ 688 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር መፈጸሙን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ እዳ ጫና ካለባቸው ሃገራት ተርታ መሰለፏን አስረድተዋል።

አሁን ላይ የሃገሪቱ እዳ 24 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከአጠቃላይ ብድሩ ውስጥ 56 ነጥብ 1 በመቶው በመንግስት ቀሪው ደግሞ በመንግስት የልማት ድርጅቶች አማካኝነት የተያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ላይ በመንግስት ያለውን ኢኮኖሚ ለማሻሻል የወጪ ቅነሳ፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ኢኮኖሚው ማስገባት እና ማክሮ ፋይናንሱ የሚመራበትን ህግ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በተጨማሪም በቴሌኮም ዘርፉ የሚስተዋለውን የጥራት፣ የተወዳዳሪነት እና የሃብት ብክነት ችግር ለመቅረፍም እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የተጀመረው ትልልቅ ድርጅቶችና ፕሮጀክቶችን በፕራይቬታይዜሽን ለማስተላለፍ የተወሰነው ውሳኔም ይህን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ የተወሰደ ነው።

በፕራይቬታይዜሽን ሂደቱ ዋናው ድርሻ በመንግስት እጅ እንደሚቆይ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከ30 እስከ 40 በመቶ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው እና ውጤታማ የሆኑ ኩባንያዎች ብቻ እንደሚይዙት እና 5 በመቶዎቹ ደግሞ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉበት እንደሚሆን ነው ያነሱት።

ዴሞክራሲውን ለማስፋት በርካታ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ለሁሉም የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ለሚሉ በራፉ ክፍት መደረጉን፣ አስረኞች እንዲፈቱ እና በይቅርታ እንዲለቀቁ መደረጉን አንስተዋል።

በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካው ለመሳተፍ ወደ ሀገር ቤት እየገቡ መሆኑን በመግለፅ ሌሎች ዘመኑ በማይፈልገው ትግል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ያሏቸው ቡድኖችም ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ነው የጠየቁት።

የሀሳብ በነፃነትን ከማጎናፀፍ አንፃርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት እንዲዘግቡ በመወሰኑ ለውጦች እየታዩ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ሆኖም የሚዲያ ሞያተኞች ሊወስዱት በሚገባው ሀላፊነት ዙሪያ ግን በቀጣይ የሚሰራ ነው ብለዋል።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.