Artificial Kidney To Replace Dialysis and Transplantation | ዳያላሲስና ንቅለ ተከላን ያስቀራል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሰው ሰራሽ ኩላሊት

በሙለታ መንገሻ

አነስተኛ መጠን ያለው እና የሰው ልጅ ኩላሊት የሚሰራውን ስራ አስመስሎ መስራት ይችላል የተባለ ሰው ሰራሽ ኩላሊት መሰራቱ ተሰምቷል።

አዲሱ ሰው ሰራሽ ኩላሊት በኩላሊት ህመም ለሚሰቃዩ በርካታ ሰዎች ህይወት አድን ሊሆን እንደሚችልም ከወዲሁ ተስፋ ተጥሎበታል።

በሰው ሰራሽ ኩላሊቱ ላይም በያዝነው የፈረንጆቹ 2018 መጨረሻ አካባቢ ሙከራ ይደረግባል የተባለ ሲሆን፥ ስኬታማ መሆን ከቻለም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚጀምር ተነግሯል።

ይህም በኩላሊት ህመም ምክንያት የሚደረገውን የኩላሊት እጥበት (ዳያላሲስ) እና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናን ሊያስቀር የሚችል እንደሆነ ነው የሚነገረው።

ጤናማ ኩላሊት በዋናነት መርዛማ ነገሮችን ከደም ውስጥ ማፅዳት፣ የሰውነታችንን የፈሳሽ ማመጣጠን፣ የደም ግፊትን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖችን ማምረት፣ የቀይ ደም ሴልን ማምረት እና የአጥንት ጤንነትን የመጠበቅ ስራዎችን ይሰራል።

ኩላሊት ህመም ተከሰተ የሚባለው ኩላሊታችን እነዚህን ተግባራት የመከወን አቅሙ ከ15 በመቶ በታች በሚወርድበት ጊዜ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ታዲያ ይህንን ለማከም ውጤታማ ነው የተባለው ህክምና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ኩላሊት ለጋሽ በቀላሉ ስለማይገኝ ህክምናውን አጋዳች ያደርገዋል።

ስለዚህ ብቸኛው የህክምና አማራጭ ዳያላሲስ ሲሆን፥ ይህ ህክምና ደግሞ ማሽን የታመመ ኩላሊታችንን በመተካት በደማችን ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ ጨው እና ከመጠን ያለፈ ፈሳሽን የሚያፀዳበት ህክምና ነው።

ዳያላሲስ ሰዎች ቢያንስ በሳምንት ከሶስት ቀናት ወደ ሆስፒታል በመሄድ ለተከታታይ ከ3 እስከ 4 ሰዓታት በማሽኑ ደማቸውን የሚያፀዱበት በመሆኑ ህክምናው ለበርካቶች አመቺ እንዳልሆ ነው የሚነገረው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ህክምናው በአነስተኛ ዋጋ የማይገኝ መሆኑ ለታካሚዎች የበለጠ ህክምናው ውስብሰብ ሲሆንባቸውም ይስተዋላል።

በእነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች የተነሳ የተፈጠረው የሰው ሰራሽ ኩላሊት በሰውነታችን ውስጥ ተተክሎ ኩላሊትን በመተካት የማፅዳት ስራን የሚሰራ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ከህክምናው ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ይቀርፋልም ተብሏል።

ሰው ሰራሽ ኩላሊቱንም የካሊፎርኒያ ሳን ፍራንሲስኮ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ናቸው የሰሩት የተባለ ሲሆን፥ በዚህ ላይ ለ20 ዓመታት መስራታቸውም ተነግሯል።

አዲሱ ሰው ሰራሽ ኩላሊት ተፈጥሯዊው ኩላሊታትን በሚሰራው መልኩ ደማችን ውስጥ ያሉ አላስፈላጊ ነገሮችን በማፅዳት፤ የፀዳውን ደማችንን ወደ ደምስራችን ቆሻሻውን ደግሞ በተገጠመለት ትቦ ወደ ሽንት ቧንቧ ያስገባል ተብሏል።

ተመራማሪዎቹ አዲሱን ሰው ሰራሽ ኩላሊት በቅርብ ወራት ውስጥ በሰው ላይ ሙከራ ማድረግ እንደሚጀምሩ ገልፀው፤ ከዚህ ቀደም በመሳሪያው በአሳማ ላይ የተደረገው ሙከራ የተሳካ እንደነበረ አስታውቀዋል።

በሰው ላይ የሚደረገው ሙከራ ስኬታማ ሆኖ ከተጠናቀቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚጀምር ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።

ምንጭ: ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement

3 Comments

Comments are closed.