NEWS: Spain Decides To Rescue Stranded Boat Refugees | ስፔን ስደተኞቹን ለመቀበል ወሰነች

የቀኝ አክራሪው ሊግ መሪና የጣሊያን የአገር ውስጥ ሚኒስትር መቲዮ ሳልቪኒ “ሲሲሊ የስደተኛ ማራገፊያ አይደለችም” ካሉ በኋላ ከእንግዲህ አገራቸው ከለላ ፍለጋ የሚመጡ ባዕዳንን ፊት እንደምትነሳ ለመራጮቻቸው ቃል ገብተው ነበር።

ይህንኑ ተከትሎ ከሰሞኑ 629 ስደተኞችን የጫነቸውን አኩዋሪየስ መርከብን ወደ ጠረፋችን ድርሽ እንዳትይ በሚል መልሕቋን እንዳትጥል ሲከላከሉ ቆይተዋል።

ግብረሰናይ ድርጅቶችን ያስቆጣው ይህ ውሳኔያቸው ስደተኞቹን ከባድ እንግልት ዳርጓቸው ነበር።

ከመቶ በላይ ሕጻናትንና ሰባት ነፍሰ ጡሮችን ጨምሮ 629 ስደተኞችን የጫነችውን ይህቺን መርከብ ከብዙ መከራ በኋላ ስፔን ለመቀበል ተስማምታለች።

ይህ የስፔን ውሳኔ ታዲያ የጣሊያኑን የአገር ውስጥ ሚኒስትር ጮቤ አስረግጧቸዋል። ትናንት በትዊተር ገጻቸው እንደጻፉት ከሆነ ይህ ለጣሊያን “ትልቅ ድል ነው” ብለዋል።

“እነሆ ድምጻችንን በትሕትና ማሰማታችን በመጨረሻ ድል አምጥቶልናል። ይህ ጣሊያን ለዓመታት ሳታደርገው የቀረችው ነገር ነበር” ሲሉ በስደተኞች ላይ መጨከን መጀመራቸው ያመጣውን ውጤት አዳንቀዋል።

በአንጻሩ አዲሱ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር የተለሳለሰ ምላሽ ሰጥተዋል። “ይህ እኮ ሰብአዊነት ነው። ግዴታችንም ነው። ይህን ባናደርግ ሰብአዊ አደጋ ይከሰት ነበር” ብለዋል።

የአውሮፓ ካውንስል የአዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ድርጊት አድንቋል።

እስከ ትናንት ማለዳ ድረስ ጣሊያንና ማልታ ስደተኞችን የጫነችውን መርከብ ላለመቀበል ሲያንገራግሩ ነበር።

ማልታ መርከቧ የምትገኘው በጣሊያን ሉዓላዊ ግዛት ስለሆነ አያገባኝም ስትል፣ ጣሊያን በበኩሏ “ሌላው አውሮፓ እጁን አጣጥፎ በተቀመጠበት ሁኔታ ጣሊያን ምን እዳ አለባት?” ሲሉ ቆይተዋል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.