“ልጄ ከአሁን አሁን ነቅቶ ይጠራኛል እያልኩ ስጠብቅ 12 ዓመት ሆነኝ”

ወ/ሮ ሀሊማ ከልጇ መሀመድ ጋር ሆስፒታል ውስጥImage copyright NEBIYU SIRAK

ወ/ሮ ሀሊማ ሙዘይን እና ባለቤቷ ኑሮን ሳኡዲ አረቢያ ሲያደርጉ ሰርቶ መኖርን ወልዶ መሳምን አስበው ነው። ከ 30 ዓመት በላይ በዚህ ሀገር ሲኖሩም ሁለት ልጆች አፍርተዋል።

ኑሯቸውን መካ ያደረጉት ሀሊማና ባለቤቷ ሁለተኛ ልጃቸው በአራተኛ አመቱ ላይ ባጋጠመው መጠነኛ የጤና እክል ጅዳ ወደሚገኝ ሆስፒታል አመሩ። “ሲተነፍስ ይቸገር ነበር በተለይ ሲተኛ መተንፈስ ያቅተው ነበር” ትላለች ወ/ሮ ሃሊማ ስለነበረው ሁኔታ ስታስታውስ።

መካ የተወለደው ልጃቸው እንደማንኛውም ሕፃን ሮጦ የሚጫወት ስቆ የሚቦርቅ ነበር። በአራተኛ አመቱ ላይ ግን የመተንፈስ ችግር ስላጋጠመው ወደ ጅዳ ለህክምና ይዘውት ሄዱ። ጅዳ ይዘውት ሲመጡ በእርሷም በባለቤቷም ዘንድ ያለው ሃሳብ ምርጡን የህክምና ክትትል አግኝቶ ወደቤቱ በሰላም ይመለሳል የሚል ነበር።

ሆስፒታሉም ይህንን ነው ያረጋገጠላቸው። አፍንጫው ውሰጥ ስጋ መብቀሉን እና እሱን ለማስወገድ የ10 ደቂቃ ቀላል ቀዶ ህክምና እንደሚያካሄዱ ተነገራቸው። ይህንን የቀዶ ህክምና ለማድረግም ከግብፃዊ ዶክተር ጋር ቀን ቆረጡ።

በቀጠሯቸው እለት ለ10 ደቂቃ የቀዶ ህክምና በሆስፒታሉ ደርሰው ሳቂታው ልጃቸውን ለዶክተሩ አስረክበው መጠባበቅ ጀመሩ።

ልጃቸው ግን ከአስር ደቂቃ በኋላ ህክምናውን አጠናቆ አልመጣም። ለሰዓታት ጠበቁ ልጃቸው ከተኛበት አልነቃም። አንድ ቀን ጠበቁ ለውጥ የለም፣ አንድ ሳምንት ከዚያም ወር ከዚያም ዓመት በልጃቸው ስጋ ውስጥ ከምትላወስ ነፍስ በቀር የጤናው ሁኔታ ሳይሻሻል ቀረ።

የ 10 ደቂቃው ቀዶ ህክምና ህይወታቸውን ባላሰቡት መልኩ አናወጠው። ከህክምናው በኋላ በሰላም ይወጣል ያሉት ልጅ ከአልጋ መነሳት አልቻለም። አይናገርም አይሰማም። ስለዚህ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል ተዛወረ። በገዛ ራሱ መተንፈስ ስላልቻለ የመተንፈሻ መሳሪያ እርዳታ አስፈለገው።

በባለቤቷ መጠነኛ ገቢ የሚኖሩት እነሃሊማ ኑሯቸው መካ እና ጅዳ ተከፈለ። እናት እና ሴት ልጇ መሀመድን ለማስታመም ጅዳ ሲቀሩ አባት ደግሞ የቤተሰቡን የእለት ጉርስ ለማሸነፍ ወደ ሥራው መካ ተመለሰ።

ኑሮ ግን በዚህ መልኩ መቀጠል አልቻለም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሴት ልጃቸው ወደ አባቷ ዘንድ ተመለሰች። ሐሊማ ልጄ ከአሁን አሁን ነቅቶ የቀድሞ ፈገግታውን አያለሁ እያለች ብቻዋን ማስታመም ቀጠለች።

”ቀሪው የቤተሰብ አባላት በሳምንት አንዴ እየመጡ ያዩታል” የምትለው ሃሊማ ልጇ ትምህርት ቤት እየሄደ ከእኩዮቹ ጋር እየቦረቀ በአካልም በመንፈስም ያድጋል ብላ ብታስብም እርሱ ግን በታመመበት አልጋ ላይ 17 ዓመት ሊሞላው ነው።

 ልጃቸውን ለ10 ደቂቃ ቀዶ ህክምና ወደ ሆስፒታል ይዘው የሄዱት እናት 12 ዓመታት በሆስፒታል ቆዩ።

በአራት ዓመቱ ለቀላል ቀዶ ጥገና ወደ ሆስፒታል የገባው መሀመድ የ17 ዓመት የልደት በአሉን በማይሰማበትና በማይለማበት የሆስፒታል አልጋ ላይ ሊያከብር ነው።

”ሆስፒታል ለቀላል ቀዶ ጥገና ከመግባቱ በፊት ሙሉ ምርመራ ተደርጎለት ጤነኛ ነው ብለዋል” የምትለው ሃሊማ ዛሬ ግን የተፈጠረውን የህክምና ስህተት የሚያስተካክል አካል ጠፍቷል።

ሆስፒታሉም ውስጥ ቀን እየገፋ ሲሄድ ልጁን ይዛ ወደቤቷ እንድትሄድ ተነግሯት ያውቃል። እርሷ ግን ልጄ በእግሩ እየተራመደ ገብቶ አልጋ ላይ የቀረው እዚሁ ስለሆነ ሳይሻለው አልሄድም በማለት እዛው እንደቀረች ትናገራለች።

ልክ እንደማንኛዋም እናት ዛሬም ልጄ ድኖ ከጓደኞቹ እኩል ወጥቶ ይገባል እያለች ተስፋ የምታደርገው ሐሊማ በአሁኑ ሰዓት ሙሉ ተስፋዋን ያደረገችው ግን በፈጣሪዋ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ

ከልጇ ጋር ሆስፒታል ላለፉት 12 አመት ማሳለፏን እያነባች የምትናገረው ሃሊማ የልጇን ነፍስ ለማቆየት የተሰካኩለት የህክምና መሳሪያዎች የተሻለ ህክምና አግኝቶ ጤናው አለመስተካከሉ እና ጉዳዩን በዲፕሎማሲም ሆነ በህጋዊ መንገድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሊረዳት ባለመቻሉ ሀዘኗን እንዳበረቱት አልሸሸገችም።

የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚገኘው ሪያድ እንደሆነ የምትናገረው ሃሊማ ሪያድ ድረስ ሄዳ ጉዳይዋን አቤት ማለቷን እንዲሁም ጅዳ ለሚገኘው ቆንስላም ማሳሰቧን ታስታውሳለች። ነገር ግን እኔ ዞር ስል ይረሱታል ስለዚህ ምንም ሊፈይዱልኝ አልቻሉም ብላለች።

በተደጋጋሚ አቤቱታ እና ውትወታ ከዘጠኝ ዓመት በኋላ ጉዳይዋን ለሀገሪቱ ጤና ጥበቃ ያቀረበችው ሃሊማ የልጇ ጤንነት አሁን ያለበት ሁኔታ ላይ የደረሰው ሙሉ በሙሉ በህክምና ስህተት እንደሆነ አረጋግጠውላታል።

መሃመድImage copyright NEBIYU SIRAK

የመሃመድን ህክምና ስህተት የመረመረው የሳኡዲ አረቢያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሀኪሞች ቦርድ ለልጇ ጤና ካሳ ይሆን ዘንድ በማለት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሪያል እንዲከፈላት ወስኖላት ነበር። በወቅቱ ሃሊማ ከብሩ ይልቅ የልጇን ጤና ስላስቀደመች አልቀበልም ማለቷን ትናገራለች።

የዚህን ውሳኔ ማህተም ያረፈበት ደብዳቤ እንኳ የኢትዮጵያ ቆንስላ መውሰድ እንዳልቻለ የምትናገረው ሃሊማ የኔ ጉዳይ በቆንስላ ውስጥ አመድ ለብሷል ስትል ታማርራለች።

ይህ ውሳኔ ከተሰጠ ሦስት ዓመት ቢሆነውም ቆንስላው ተከታትሎ ማስፈፀም እንዳልቻለ እንዲሁም የሚገባትን ካሳ ማግኘት እንዳልቻለች ትናገራለች።

በሳኡዲ አዲስ ህግ ወጥቷል የምትለው ሃሊማ በዚህ ህግ መሰረት ለልጇ ህክምና መክፈል ይጠበቅባታል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለልጇ መክፈልም ሆነ የጤናውን ሁኔታ መከታተል ስላልቻለች የተወሰነላትን ክፍያ አግኝታ ወደ ሃገሯ መግባት ትፈልጋለች።

“ዓለም መከራ ናት” የምትለው ሃሊማ አሁን ልጇን ዶ/ር አይከታተለውም ነርስም አልተመደበለትም። ሕልሜ በሌላ ሀገር የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ እና እንዲድን ነበር ትላለች።

”ከዚህ ውጭ ግን የልጄን ጤንነት የነጠቀው ዶ/ር ተቀጥቶ፣ ያወጣሁት ወጪ ተከፍሎኝ እና ለደረሰብኝ ስቃይ ተክሼ ወደ ሀገር ቤት ብገባ እና ልጄን ለሀገሬ አፈር ባበቃው ምኞቴ ነው” ትላለች ከማያቆመው እንባዋ ጋር እየታገለች።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ኑሯቸውን በሳኡዲ ያደረጉት አቶ ነብዩ ሲራክ የሃሊማን ልጅ ታሪክ ከሰሙ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

የሃሊማ ታሪክ በህግ በአግባቡ ቢያዝ እና የሚከታተልላት አካል ቢኖር 12 ዓመት ሥራ መፍታቷ፣ ያወጣችው ወጪ ተሰልቶ እስከ 15 ሚሊዮን የሳኡዲ ሪያል ሊከፈላት ይችላል ይላል። ነገር ግን ብቸኛ መሆኗ እና የሚከታተልላት ወገን መጥፋቱ ፈተናዋን እንዳበረታባት ይናገራል።

ምንጭ:  ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.