ዶክተር ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ የ62 ግለሰቦች ክስ ተቋረጠ

ተከሳሾቹ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ ተከላከሉ ተብለው እንደነበር ይታወቃል።

የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ፤ በእነ አበበ የኋላ የክስ መዝገብ የተጠቀሰውን አንቀጽ በመተላለፍ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ያሉ 18 ተከሳሾች ክስም እንዲነሳ ተወስኗል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዶክተር ፍቅሩ ማሩ ጠበቃ አቶ አበበ እሸቴ እንዳሉት ደንበኛቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ያገኟቸው ግንቦት 1 ፍርዱ የተላለፈ ዕለት እንደሆነና በዛሬው ውሳኔውም መደሰታቸውን ገልፀዋል።

በቅርቡ መንግስት የጀመረው የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ሂደት በተቆራረጠ ሁኔታ መፈፀሙ አሳስቧቸው እንደነበር ይናገራሉ።

ደንበኛቸው አቶ ፍቅሩ ማሩን ጨምሮ ዛሬ ክሳቸው የተቋረጠላቸው 62 ተከሳሾች ጉዳይ ይህን ያህልም መዘግየቱ በህገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን የማንኛውም ሰው ከመድሎ ነጻ የመሆን መብት የሚጋፋ ነው እያሉ ሲከራከሩ እንደነበር ይናገራሉ አቶ አበበ።

የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ይድነቃቸው ከበደ ደግሞ ዛሬ ክሳቸው ከተቋረጠላቸው 62 ተከሳሾች መካከል ሰላሳዎቹ የሰማያዊ ፓርቲ አባል መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ አይነት ክስ አባሎቻቸው ላይ እንደሚቀርብ ነገር ግን ዛሬ የሰሙት የክስ መቋረጥ ዜና እንዳስተደሰታቸው ገልፀዋል።

እርምጃው ለወደፊቱም ጥሩ ጅምር ይሆናል የሚል እምነትም አላቸው።

በእነ ማስረሻ ሰጠኝ መዝገብ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ጉዳያቸው ሲታይ ከነበሩት 38 ተከሳሾች ደግሞ፤ አራቱ በሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው እንዲከላከሉ፤ስምንቱ ግን በነጻ እንዲሰናበቱ መወሰኑ ይታወሳል።

በተጠቀሰው መዝገብ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 464 እና 494 በመተላለፍ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ቀሪ 26 ተከሳሾች ክስ ደግሞ እንዲነሳ ተወስኗል።

በሰው መግደል ወንጀል እንዲከላከሉ የተበየነባቸው የአራቱ ተከሳሾች የፍርድ ሂደት ግን ባለበት ይቀጥል ተብሏል።

ምንጭ: ቢቢሲ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.