ዜና እረፍት: የአፍቃሪ ኢትዮጵያው ቤተሰብ የመጨረሻ ሰው፣ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ አረፉ::

እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ እ.ጎ.አ በመጋቢት 5 ቀን 1935 የተወለዱት ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ አባታቸው የሙዚቃ ሊቅ እናታቸው ደግሞ የአባታቸው የሙዚቃ ተማሪ ነበሩ፡፡ አፍቃሪ ኢትዮጵያ የሆኑት የፕሮፌሰር አብይ ወላጆች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በ1923 የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የዘውድ በዓል ለማክበርና ለኢትዮጵያም የተቻለውን ለማድረግ በሚል ከመጣው የካሪቢያን ቡድን አባላት ጋር በመሆን ነበር፡፡

ጥንዶቹ ትዳር መስርተው ዮሴፍ ኃይለሥላሴ ፎርድን እና አብይ ፎርድን ወልደው ኢትዮጵያ ውስጥ ኑሯቸውን ቀጠሉ፡፡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ የተከታተሉት ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ በአሜሪካ በፓኔ ውድስ ጁኒየር ኮሌጅ በኢለመንታሪ ኢዱኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ከዚያም ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሰቲ ስኩል ኦፍ ጀኔራል ስተዲስ በፊልም ጥናቶች የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

በሃዋርድ ዩኒቨርስቲም የሙሉ ፕሮፌሰርንትን ማዕረግ እስካገኙበት ጊዜ ድረስ ለ33 አመታት ያህል አገልግለዋል፡፡

ሮፌሰር አብይ ፎርድ የቀድሞው የአ.አ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮምኒኬሽን የድህረ ምረቃ ት/ቤት ዲን፤ የዩኒቨርስቲው ፐሬዚዳንት ፅ/ቤት ከፍተኛ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ26 የሚበልጡ ዶክመንታሪ ፊልሞችንም ሰርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኘው፣ ተከታታይ ትውልዶች የተማሩበት በፕሮፌሰር አብይ ፎርድ እናት የተሰራው ሚስስ ፎርድ መታሰቢያ የአፀደ ህፃናት እና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የዚህ አፍቃሪ ኢትዮጵያ ቤተሰብ መታሰቢያ ሆኖ አሁንም ድረስ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡

በፋሽስት ወረራ ጊዜ የውጭ ሐገር ዜጎች ኢትዮጵያን ጥለው ሲወጡ የፕሮፌሰር አብይ ፎርድ ቤተሰቦች ግን ኢትዮጵያን በችግሯ ጊዜ ጥለን አንሄድም ብለው እዚሁ ቆይተዋል፡፡

የፕሮፌሰር አብይ አባት በሚወዷት ኢትዮጵያ ነው ኖረው፣ ሞተው የተቀበሩት፡፡

እናታቸው ሚስ ፎርድም ልጆቻቸውን ለመጠየቅ አሜሪካ ሄድው ህይወታቸው እዚያ ቢያልፍም መቃብራቸው ግን ኢትዮጵያ ሆኗል፡፡ የፕሮፌሰር አብይ ፎርድ ወንድምም በተመሳሳይ አሜሪካ ሞተው በኢትዮጵያ መሬት ነው ያረፉት፡፡

እነሆ በዛሬው ዕለት የሚስ ፎርድ ቤተሰብ፣ የዚህ አፍቃሪ ኢትዮጵያ ቤተሰብ የመጨረሻው ሰው ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ በአሜሪካ ሐገር ማረፋቸውን ሰማን::

ነፍስ ይማር!

ምንጭ: የሸገር FM 102.1 ሬዲዮ

Advertisement

1 Comment

Comments are closed.