ፈረንሳይ ስደተኞችን የተመለከተ ጥብቅ ሕግ አወጣች

                  

የፈረንሳይ ብሄራዊ ምክር ቤት በጥገኝነት ጠያቂዎች ዙሪያ ያለውን ደንብ የሚያጠብቅ ጠንካራ የስደተኞች ሕግ አፀደቀ።

ሕጉ ጥገኝነት ለሚጠይቁ ሰዎች ጥያቄ የሚያቀርቡበትን የጊዜ ገደብ ያሳጠረ ሲሆን ሕገ-ወጥ ስደተኞች ሊታሰሩ የሚችሉበትን ጊዜ በእጥፍ እንዲጨምር አድርጓል። በተጨማሪም ወደ ፈረንሳይ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚገቡ ስደተኞች አንድ ዓመት እንዲታሰሩ የሚያደርግ አዲስ ቅጣትንም አካቷል።

የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ገዢ ፓርቲ እንዳለው አዲሱ ሕግ ያለውን ጥገኝነት የመጠየቂያ ሂደት ያፋጥነዋል።

ነገር ግን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች እንደሚሉት በሕጉ ላይ ያሉ እርምጃዎች ከተገቢው በላይ የተጋነኑ ናቸው ብለዋል።

ይህ አዲስ ሕግ በ228 ድጋፍ፣ በ139 ተቃውሞና በ24 ድመፀ ተአቅቦ ማለፉም ተዘግቧል።

በመቶ ዎች የሚቆጠሩ ማሻሻያዎች ከቀረቡበት በኋላ ነበር ሕጉ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ድምፅ የተሰጠበት።

አንድ የፕሬዝዳንት ማክሮን ፓርቲ አባል አዲሱን ሕግ ተቃውመው ድምፅ የሰጡ ሲሆን 14 የሚሆኑት ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዋች የተባለው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት እንዳለው ጥገኝነት የመጠየቂያውን ጊዜ ማሳጠር “ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች በተሰጠው ጊዜ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ስለማይችሉ ጊዜው እንዲያልፍባቸው ሊያደርግ ይችላል” በማለት አዲሱ ሕግ አሉታዊ ውጤት ሊኖረነው እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

“ውጤታማ የጥገኝነት መጠየቂያ ሥርዓት በመዘርጋት ስም አዲሱ ሕግ ጥበቃ የማግኘት ዕድልን የሚያጠቡ ተከታታይ እርምጃዎችን አካቷል” ሲሉ የሂዩማን ራይትስ ዋች የፈረንሳይ ዳይሬክተር ቤኔዲክት ጂያኔሮድ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

አዲሱ ሕግ በመጪው ሰኔ ወር ላይ ለፈረንሳይ የላይኛው ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።

ማስታወሻ በስያሜ ላይ፡ ቢቢሲ ስደተኛ የሚለውን ቃል የሚጠቀመው ከሃገራቸው ወጥተው ጥገኝነት ለማግኘት የሚያስፈልገው ሕጋዊ ሂደት ላይ ላሉ ሰዎች ነው። በእዚህ ውስጥም ሶሪያን ከመሳሰሉ በጦርነት ውስጥ ካሉ ሃገራት የሚመጡትንና ሌሎች ደግሞ መንግሥታት የኢኮኖሚ ስደተኞች የሚሏቸውን ሥራና የተሻለ ህይወትን ፍለጋ የሚሰደዱትን ያካትታል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement