የተመድ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራአድ ከእሁድ ጀምሮ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ

                 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራአድ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።

ኮሚሽነሩ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ መንግስት ባደረገላቸው ግብዣ መሰረት እንደሚመጡም ታውቋል።

የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራአድ ከእሁድ ጀምሮ አራት ቀናት በሚያደርጉት ጉብኝትም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ተገናኝተው የሚወያዩ ይሆናል።

በተጨማሪም ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ከሲቪክ ማህበራት ተወካዮች እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩም ይጠበቃል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት እና በተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በሚያደረጉት ውይይት ላይም እንደሚካፈሉም ተነግሯል።

ከውይይቱ በኋላም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት እና እና የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዘይድ ራአድ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚሰጡ ይሆናል።
ኮሚሽነሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመገኘትም በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪያ እንደሚሰጡም ይጠበቃል።

የተመድ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነሩ ዘይድ ራአድ ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በወቅቱም በኢትዮጵያ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ ዙሪያ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ስላለው የሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይም ከምስራቅ አፍሪካ ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ኮሚሽነሩ ከፊታችን እሁድ ጀምሮ ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝትም በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ግብዣ የሚደረግ መሆኑን ተመድ አስታውቋል።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement