የቻይና ኢኮኖሚ ከተገመተው በላይ እድገት ማስመዝገቡ ተነገረ

                  

የቻይና ኢኮኖሚ በአውሮፓውያኑ 2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከተገመተው በላይ እድገት ማስመዝገቡ ተነገረ።

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር ወር እስከ መጋቢት ወር ባለስ ሶስት ወራት ውስጥ የ6 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ነው ያስመዘገበው።

ይህም በሩብ ዓመቱ ይመዘገባል ተብሎ ከተገመተው የ6 ነጥብ 5 በመቶ እድገት ብልጫ ማሳየቱ ነው የተነገረው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዓለማችን ሁለተኛ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ቻይና የኢኮኖሚ እድገቷ ቀጣይነት እንዲኖረው ካደረጉት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የሸማቾች ፍላጎት አንዱ መሆኑ ተጠቅሷል።

ሆኖም ግን የእዳ መጠን ከፍ ማለት እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ወደፊት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊጎዱ ይችላሉ የሚሉ ሀሳቦችም ተነስተዋል።

የሀገሪቱ መንግስትም ከፍ ያለውን የእዳ መጠን እና በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤቶች ችግርን እድገቱን በማይጎዳ መልኩ ለማስተካከል እየታገለ መሆኑ ነው የተነገረው።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement