ክብደት ማንሳትንጨምሮ የሰውነት ማጠንከሪያ ስፖርቶች ያለ እድሜ የሚከሰት ሞትን በ46 በመቶ ይቀንሳሉ

           

ክብደን ማንሳትን ጨምሮ የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን አዘውትሮ መስራት ያለ እድሜ የሚከሰት ሞትን በ46 በመቶ ይቀንሳሉ ተባለ።

የፔን ስቴት የህክምና ኮሌጅ ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት እንደያሳየው፤ በተለይ ሰዎች እድሜያቸው እየገፋ በሄደ ቁጥር እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ የሰውነት ማጠንከሪያ ስፖርቶችን መስራት ያለወቅት የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ ይረዳል።

ጥናቱ እድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ የተካሄደ ሲሆን፥ ምን አይነት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንደሚያዘወትሩ በመለየት ለ15 ዓመታት ክትትል ተደርጎባቸዋል።

በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ውስጥ አንድ ሶስተኛው በክትትል ወቅት ህይወታቸው ማለፉም ተገልጿል።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለፃ በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ወስጥ ከ10 በመቶ በታቹ ብቻ የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሰሩ መሆኑም ተለይቷል።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች ውስጥም የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚሰሩ ሰዎች ከሌሎች ጋር ሲነጻጸሩ ቶሎ የመሞት እድላቸው በ46 በመቶ ቀንሶ ታይቷል ነው ያሉት ተመራማሪዎች።

የጥናቱ ፀሃፊ ዶክተር ጄኒፈር ክራስቸኔወስኪ፥ እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴወች እድሜያችን እየገፋ በሄደ ቁጥር ንቁ እና በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዳንሆን ያደርጋል ብለዋል።

እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ጡንቻን ከማጠንከር በዘለለ ሚዛናችንን እንድጠብቅ እና የአጥንታችን ጥንካሬ እንዲጨምርም ያደርጋሉም ብለዋል።

እነዚህ አንድ ላይ ተደምረው እድሜያችን በሚገፋበት ጊዜ ድንገት በምንወድቅበት ጊዜ የሚደርስብን የመሰበር አደጋ ይቀንሳል ተብሏል።

የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እቅስቃሴ መስራትን መጀመር ይፈልጋሉ?

እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማንኛውም ሰው ቢሰራቸው ምንም ችግር የለበትም።

እድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆነ እና ከዚህ ቀደም እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ሰርተው የማያውቁ ሰዎች ግን መጀመሪያ የጤና ባለሙያ ማማከር ይኖርባቸዋል ነው የተባለው።

ነገር ግን ያለንበት የእድሜ ክልል እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ የሰውነት ማጠንከሪያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ከመስራት ያግደናል ብለው አያስቡ ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement