በማስታገሻ ብቻ የሚታከሙ እስረኞች

                    

እስረኞች ችሎት ላይ ከሚያሰሟቸው አቤቱታዎች ህክምና ማግኘት አለመቻል ዋናው እንደሆነ ቀደም ሲል ታስረው የነበሩና የፍርድ ቤት ውሎ ዘጋቢ ጋዜጠኞች ይናገራሉ።

እነሱ እንደሚሉት በአንደኛ ደረጃ የሚቀርበው አቤቱታ ቀጠሮ ረዘመብን ሲሆን ህክምና ማግኘት አልቻልንም የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ነው።

ከቅርብ ጊዜዎቹ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ሊቀመንበሩ አቶ በቀለ ገርባ በእስር ሳሉ የአይን ህክምና ማግኘት አለመቻላቸውን በተመለከተ ያሰሙት አቤቱታ ሊጠቀስ ይችላል።

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ምንም እንኳ ከባድ የጀርባ ህመም የነበረበት ቢሆንም ህክምና እንዳላገኘ ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ተናግሮ ነበር።

ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለታሰሩ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም እስረኛ ይሄኛው ያኛው እስር ቤት ሳይባል ህክምና ማግኘት ከባድ እንደሆነ ያነጋገርናቸው ያስረዳሉ።

ከአመታት በፊት ከሙስና ጋር በተያያዘ የታሰሩት የአዲስ ካርዲያክ ሆስፒታል ባለቤት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩም ከህክምና ጋር በተያያዘ አቤቱታ አሰምተው እንደነበር ይታወሳል።

ህመም ማስታገሻ-ዋናው ህክምና

ጫልቱ ታከለ ከአመታት በፊት የሃገርን ፖለቲካና ግዛት አንድነት በመንካት በሚል ተከሳ 12 አመት ተፈርዶባት 8 ዓመት ከ45 ቀን ታስራ በአመክሮ ወጥታለች።

እንደገና በሽብር ተከሳ 11 ወር ከታሰረች በኋላ መንግስት በቅርቡ እስረኞችን ሲለቅ እሷም ክሷ ተቋርጦ ከእስር ወጥታለች።

2001 ዓ.ም ላይ ከነበረችበት ማእከላዊ ወደ ቃሊቲ ስትዘዋወር ህክምና ማግኘት እንደምትፈል መጠየቋን ታስታውሳለች።

“ማእከላዊ ጆሮዬን ተመትቼ ስለነበር በጣም ያመኝ ይደማም ነበር” የምትለው ጫልቱ ምንም እንኳ የፖለቲካ እስረኞች ላይ ነገሩ ቢከፋም በጤና ጣቢያ ወይም በሆስፒታል ህክምና ማግኘት ለማንኛውም እስረኛ ከባድ እንደሆነ ትናገራለች።

እሷ እንደምትለው የቱን ያህልም ህመማቸው የበረታ ቢሆን እስረኞች በተደጋጋሚ የህመም ማስታገሻ እንዲወስዱ እንጂ በቀላሉ ሪፈር አይፃፍላቸውም።

እሷም በተመሳሳይ መልኩ ህመም ማስታገሻ ወስዳ ሊሻላት ስላልቻለ በተደጋጋሚ ጠይቃ በመጨረሻ የካቲት 12 ሆስፒታል እንድትታከም መደረጉን ትናገራለች።

“የሞት ወይም እድሜ ልክ ፍርደኛ ለሆነ የፖለቲካ እስረኛ ወጥቶ በመንግስት ሆስፒታል መታከም የሚታሰብ አይደለም።ሪፈር መፃፍ ይፈራሉ።”ትላለች።

እሷ እንደምትለው ሪፈር ቢፃፍላቸው እንኳ አጃቢ ፖሊስ ወይም መኪና የለም በሚል ምክንያት ሳይሄዱ ይቀራሉ።ከሄዱም ሃኪም ጋር ሲቀርቡ እንኳ አጃቢ ፖሊስ አብሯቸው እንዲገባ ይደረጋል።

ይህ ደግሞ እንደ ታካሚ ነፃነት እንዳይሰማቸው ያደርጋል ፤ ሃኪሞችንም ምቾት ይነሳል።

ኒሞና ጥላሁን የሚባልና የካንሰር ህመምተኛ ጓደኛቸው ዛሬ መኪና ነገ አጃቢ ፖሊስ የለም በሚል የኬሞ ቴራፒ ህክምናውን በአግባቡ መከታተል አለመቻሉን ታስታውሳለች።

“ኬሞ ቴራፒውን ባግባቡ መውሰድ አለመቻሉ ሞቱን አፋጥኖታል ብዬ አምናለሁ። ስፔሻሊስት ሊያያቸው ይገባል የተባሉ እስረኞችም ሃኪሞቹ በሚገቡበት ቀን የመወሰድ እድላቸው በጣም አነስተኛ ነው።ምክንያቱም መኪና ወይም አጃቢ ፖሊስ የለም ይባላል።” ትላለች።

ለወሊድ በቀላሉ ሪፈር የሚፃፍ ቢሆንም አጃቢ ፖሊስ ወይም መኪና የለም በሚል ምክንያት የቅድመ ወሊድ ክትትል ግን የማይታሰብ እንደሆነ ትገልፃለች።

ለሷ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በሚገኘው ክሊኒክ የመታከም ምንም ችግር ያልነበረ ቢሆንም የክሊኒኩ ባለሙያዎች ግን ብቃት ያላቸው እንዳልሆኑ ትናገራለች።

የጥርስ ህመምን በምሳሌነት በማንሳት “ጊዜ የማይሰጠው የጥርስ ህመም እንኳ እዚያ ክሊኒክ ነው የሚታከመው።እስኪ ይሄን ያን እያሉ በመሰላቸው መንገድ የተለያዩ ህመም ማስታገሻዎችን እስረኞች እንዲወስዱ ያደርጋሉ።በጣም ብዙ ጊዜ የህመም ማስታገሻ ተወስዶ ነው ወደ ጥርስ ህክምና መሄድ የሚፈቀደው”ትላለች።

ከማህፀን ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ሴቶች ሲመረመሩ አጃቢ ፖሊሶች አብረው እንደሚገቡና ይህ በጣም ነፃነታቸውን እንደሚጋፋ ጫልቱ ትገልፃለች።

“እድሜ ልክ ወይም የሞት ፍርደኛ ከሆንሽ አጃቢ ፖሊሶች ቀዶ ህክምና ክፍል ሁሉ ይገባሉ”ትላለች።

“አሞክሳ”

በሽብር ተጠርጥሮ ታስሮ የነበረውና ከተፈታ በኋላ በተለይም የፖለቲካ እስረኞችን የችሎት ውሎ እየተከታተለ በመፃፍ የሚታወቀው ጌታቸው ሽፈራውም ለስረኞች ህክምና ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራል።

በመሰረታዊነት የህክምና ችግር ፤ የመድሃኒት እጥረት ቢኖርም ለፖለቲካ እስረኞች ግን በተለየ መልኩ ህክምና ማግኘት በጣም ከባድ እንደሆነ ይናገራል።

“ማእከላዊ ፣ቃሊቲ ፣ዝዋይና ቂልንጦም ነበርኩ” የሚለው ጌታቸው ሁሉም ጋር ይህ ነው የሚባል ህክምና እንደሌለ ይገልፃል።


ከቂሊንጦ ወደ ዝዋይ ሲዘዋወሩ ሃኪሞች ታመምን ያሉ እስረኞችን አይን በማየት የተለየ ነገር ላዩበት እስረኛ ብቻ መድሃኒት ይሰጡ እንደነበር ያስታውሳል።

እንደ ጫልቱ ጌታቸውም ለእስረኞች ዋናው ህክምና የህመም ማስታገሻ እንደሆነ ይናገራል።

እሱ እንደሚለው ከማስታገሻ ሲያልፍ ደግሞ የሚሰጠው መድሃኒት አሞክሳሲሊን ነው።እስረኞች የታሰሩበት እስር ቤት ውስጥ ወዳሉ ክሊኒኮች ሲሄዱ የሚሰጣቸው አሞክሳሲሊን እንደሚሆን በርግጠኝነት እንደሚገምቱ ሁሉ ይገልፃል።

በዚህ የተነሳም አሞክሳሲሊን በእስረኞች ዘንድ “አሞክሳ” እየተባለ ይጠራል።

“የተወሰነ ሰው እንደገባ ለዛሬ በቃ ከዚህ ወዲህ ሁሉ ይባላል።”

እስር ቤቶቹ ውስጥ ባሉ ሰራተኞች የተከሰሰ ሰው ሁሉ ወንጀለኛ ነው የሚል አመለካከት መኖርም ሌላው ችግር ነው ይላል። ጌታቸው።

ጌታቸው እንደሚለው የምግብ ጥራት ችግርና ተፋፍጎ አንድ ቦታ ላይ መተኛት ራሱ እስረኛውን ለተለያየ ህመም ያጋልጣል።

“ቂሊንጦ 160 ምናምን የሚሆን ካሬ ላይ 150 የሚሆን እስረኛ ይታሰራል።”የሚለው ጌታቸው በዚህ ላይ ህክምና ማግኘት አለመቻል እጅግ ፈታኝ እንደሆነ ያስረዳል።

ህግና መሬት ላይ ያለው እውነታ

እስረኞች እንዴት መስተናገድ አለባቸው የሚለው በህግ ታራሚዎች ህግ መሰረት መፈፀም ቢኖርበትም የሚታየው እውነታ ግን ህጉ ከሚለው የተለየ እንደሆነ የበርካታ ፖለቲካ እስረኞች ጠበቃ የሆነው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ይናገራል።

እስሯን ጨርሳ የወጣችውና በማህበራዊ ድረ ገፆች የጤናዋ ሁኔታን በተመለከተ መነጋገሪያ ሆና የነበረቸው ቀለብ ስዩም ጠበቃም ነበር አቶ ሄኖክ።

አቶ ሄኖክ ጥብቅና ከቆመላቸው መካከል በቅርቡ ከስር የተለቀቀችው ንግስት ይርጋ፣ የቀድሞ የመኢአድ አመራር አቶ ማሙሸት አማረ ይገኙበታል።


ጠበቃ ሄኖክ እንደሚለው እስረኞች አብዛኛውን ጊዜ እንዲታከሙ የሚደረገው ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ባሉ ጤና ተቋማት ሲሆን በዚያ ያለው ዋናው ነገር ደግሞ ህመም ማስታገሻ ነው።

“ከማረሚያ ቤቱ ውጭ እንዲታከሙ ሪፈር የሚፃፍላቸው ብዙ ከዘገየ ስለሚሆን በቀላሉ የሚታከም ህመም ከባድ ደረጃ ላይ ይደርሳል።በዚህ መልኩ የጤናቸው ነገር አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሶ የሞቱ ሁሉ አሉ”የሚለው ሄኖክ የፖለቲካ እስረኛ መሆን ደግሞ ሌላ የራሱ ፈተና እንዳለው ያስረዳል።

እሱ እንደሚለው በፖለቲካ በተለይም በሽብር ተጠርጥረው የታሰሩ ህክምና ማግኘት እንደሚፈልጉ ሲናገሩ በህክምና ባለሙያዎች ሳይቀር “አንተ/ችማ በሽብር ነው የታሰርከው” ብሎ የመፈረጅና የማግለል ነገር አለ።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን በስልክ ማግኘት ብንችልም በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈለጉም።

Advertisement