ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በአምቦ ከተማ ያደረጉት ጉብኝት

                 

በሺዎች የሚቆጠሩ የአምቦ እና የአከባቢዋ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በተዘጋጀው ስነ-ስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አባላት ተሳታፊ ነበሩ።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ለተሳታፊዎቹ ባደረጉት ንግግር ፣”በኢትዮጵያ ህዝቦች እና በድርጅታችን የተሰጠንን ተልዕኮ ለማሳካት ያለንን ቁርጠኝነት ለመግለጽ እዚህ ተገኘተናል፤” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም፣ በወጣቶች እና በሴቶች ለበርካታ ዘመናት ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎች እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው እና ለእነዚህ ጥያቄዎች መፍትሄ እንደሚያፈላልጉ ተናግረዋል።

“ያለ ወጣቶች እና ሴቶች ተሳትፎ አስተማማኝ ሰላምን ማረጋጋጥ፣ ዲሞክራሲን ማስፈን እና ቀጣይነት ያለው ልማትን ማረጋገጥ አይቻልም፤” ሲሉም ጠቅላይ ሚንስትሩ ተደምጠዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለክልሉ ህዝብ አንድነትን በተመለከተ ጥሪ አቅርበዋል።

”የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከር ለሌሎች የሃገራችን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች መልካም አርዓያ መሆን አለበት፤ ለዚህም የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ ነው፤” ብለዋል።

የአምቦ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳባ ጩፋ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ አምቦ መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረው፣ ”ጠቅላይ ሚንስትሩ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ያደረጉትን ንግግር በተግባር እንዲፈጸሙ እንጠብቃለን፤ ለዚህም በቂ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል፤”ብለዋል።

”ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ዕድልም ፈተናም ይጠብቃቸዋል፤” ያሉት አቶ ዳባ፣ “ፈተና ሊሆንባቸው የሚችለው ብዙ ጥያቄዎች ያሉትን ህዝብ ይዞ ወደ ፊት መጓዝ ሲሆን እንደ ዕድል የቆጠሩት ደግሞ ህዝቡ ለለውጥ ተነሳሽ መሆኑ ነው፤” ሲሉም አክለዋል።በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ቦንቱ ደቀባ በበኩሏ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ብዙ እንደምትጠብቅ ትናገራለች። በተለይ ወጣቱ ከድህነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ሲያነሳ መንግሥት በጥይት ሳይሆን ህግን በተከተለ መልኩ ማስተናገድ እንዳለበት እና ይህንንም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደምትጠብቅ ገልጻለች።

ሌላኛው ቢቢሲ ያናገረው ወጣት አዳነ አበበ ፣”ወጣቱ ፀረ-ዴሞክራሲ ሳይሆን እንደውም ዴሞክራሲን የሚያበረታታ ነው፤ ስለዚህ መንግስት ወጣቱን እንደ አልሸባብና አልቃይዳ መመልከት ሳይሆን መብቱን እየጠየቀ መሆኑን ተረድቶ ጥያቄውን በአግባቡ ሊያስተናግድለት ይገባል፤” ይላል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement