“ውሳኔው የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የጋራ ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ

                  

ሃውስ ሪዞሉሽን 128 የተባለውና የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ጫና ያሳርፋል ተብሎ የሚጠበቀው ሰነድ በ108 የኮንግረስ አባላት ድጋፍ ትናንት መፅደቁን ተከትሎ በተለያዩ አካላት ዘንድ መወያያ ሆኗል።

ይህ ሪዞሉሽን ከዚህ ቀደም ከነበሩት ኤችአር 2003 እንዲሁም ኤችአር 2006 የተለየ እንዳልሆነና እነዚህም ውሳኔዎች የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ የሚናገሩ ወገኖች ሲኖሩ፤ በተቃራኒው ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘት እንዲህ አይነት ውሳኔ ሲያልፍ የመጀመሪያው በመሆኑ ፖለቲካዊው አንድምታ ሊታይ ይገባል የሚሉ አካላት አሉ።

ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ በሀገሪቷ ውስጥ በጥቁሮች ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፤ እንዲሁም በተለያዩ አገራት ላይ በምታደርሳቸው ቁጥር የለሽ ጥቃቶች የተነሳ ስለ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ መብት አያያዝ የመተቸት የሞራል የበላይነት የላትም የሚሉም አልታጡም።

ይህ ውሳኔ በተለይ በአሜሪካ የሚኖሩና ውሳኔው እንዲያልፍ ሲወተውቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ጮቤ ያስረገጠ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።

የመንግሥት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ውሳኔውን ” የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነትና የጋራ ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም” ብለውታል።

ውሳኔው በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው የሚናገሩት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ “ወቅታዊም አይደለም ተገቢ ውሳኔ ነው ብለን አናየውም” ብለዋል።

እንደ ምክንያትነት የሚያስቀምጡትም ኃገሪቷ ላይ ለነበሩት ችግሮች መንግሥት ተጠያቂነትና ኃላፊነት በመውሰድ መፍትሄ ለመስጠት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀዋል።

“ኢትዮጵያና አሜሪካ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው። ለቀጠናው አስተዋፅኦ እያደረግን ነው። እነዚህን ሁሉ ጥረቶች ወደ ጎን በመተው፤ እንዲሁም በሁለቱ ኃገራት መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ከግንዛቤ ያላስገባ ውሳኔ ማሳለፍ ተገቢ አይደለም።” ብለዋል።

ውሳኔው ቀላል ( ሲምፕል ሪዞሉሽን) የሚባለው ሲሆን ምንም አይነት የህግ አፈፃፀም እንደሌለው ተገልጿል። ይህንንም አስመልከቶ ዶ/ር ነገሪ አስፈፃሚው አካል የደገፈው እንዳልሆነና ወደ ሌላ ተፅእኖም የሚሸጋገር እንዳልሆነም ይናገራሉ።

” የኮንግረስ አባላቱ አቋማቸውን መግለፃቸው መብታቸው እንደሆነም እናውቃለን። በኛ በኩልም ይህ ውሳኔ የሚያመጣው ለውጥ የለም” የሚሉት ዶ/ር ነገሪ “ሌላ አካል ነግሮን ሳይሆን ህዝባችን እንዲሁም ህገ-መንግሥቱ ስለሚያስገድደን መንግሥት እየሰራቸው ያሉ መጠነ-ሰፊ ማሻሻያዎች አሉ ይህ ደግሞ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል” ብለዋል።

የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው ሰነዱን ለኮንግረስ አባላት ካቀረቡት እንዲሁም ሲወተውቱ ከነበሩት አካላት ጋር ተነጋግረው እንደነበር አውስተው የዚህ ሰነድ መፅደቅ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ ሂደት ላይ ለውጥ ያመጣል ብለው ያምናሉ።

በእርግጥ በውጭ መንግሥት ተፅእኖ ብቻ በሀገር ውስጥ ለውጥ ይመጣል ብለው ባያስቡም ይህ ሪዞሉሽን የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መቆሙን ማሳያ ነው ብለዋል።

“አንድ ሀገር ሌላኛውን ሀገር ነፃ አውጥቶ አያውቅም። ግን እንደ ሀገር ደግሞ ከዓለም የተነጠልን አይደለንም፤ የአለም አካል ነን። አለም ላይ ያሉ ተቋማት ሰብአዊ መብትን የሚረግጥን ድርጅት ወይም አገዛዝ የሚቃወሙ ተቋማት ከጎናችን ሊቆሙ ይገባል” ይላሉ።

በአሜሪካ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ ገዳሙ ይህ ውሳኔ ለለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን መልካም ዕድል እንደሆነ ይናገራሉ።

የዚህ ሪዞሉሽን መፅደቅ አስገራሚ ነው የሚሉት ዶ/ር ዮሀንስ ለዓመታት በኢትዮጵያና በአሜሪካ መንግሥታት መካከል ያለው ጥገኝነት ጥብቅ ነው ተብሎ ስለሚገመትና የአሜሪካ መንግሥትም በስልጣን ላይ ያለ አገዛዝ ደጋፊ ተደርጎ የሚታይበት ሁኔታ ከፍተኛ ስለነበረ እንደሆነ ይገልፃሉ።

“ይህ ሪዞሉሽን ለኢትዮጵያውያን የለውጥ ፍላጎት በተለይም ሀገሪቷ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሸጋገር፤ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች እንዲቆሙና የፖለቲካ እስረኞች ሙሉ በሙሉ እንዲፈቱ፤ በአጠቃላይ ሁሉን አቀፍ የሆነ ስርዓት የሚመሰረትበትን መንገድ ከመጥረግ አንፃር ትልቅ ሚና ሊኖረው ይችላል ብየ አስባለሁ” ብለዋል።

ጨምረውም “አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃልኪዳናቸውን ወደ ተግባር መቀየር የሚፈልጉ ከሆነ ከኢትዮጵያውያን አሜሪካውያንና ከአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር ሆኖ መታየት አለበት” ብለዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement