ቻይናዊው ሕፃን ቤተሰቦቹ ከሞቱ ከአራት ዓመታት በኋላ ተወለደ

                 

ቻይና ውስጥ አንድ ሕፃን ቤተሰቦቹ ከሞቱ ከአራት ዓመታት በኋላ መወለዱ ብዙዎቹን አጀብ አሰኝቷል።

ቤተሰቦቹ ከአራት ዓመታት በፊት ነበር በመኪና አደጋ ምክንያት የሞቱት።

ቤተሰቦቹ ሕይወታቸውን ያጡት በአውሮፓውያኑ 2013 ሲሆን ከመሞታቸው በፊት ነበር የዘር ፍሬዎቻቸውን ማቀዝቀዣ ውስጥ ያኖሩት።

የሟቾቹ ወላጆች በበኩላቸው ‘የዘር ፍሬውን ተጠቅመን የልጅ ልጅ ማየት ይገባናል’ በማለት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደውት ነበር።

ከብዙ ክርክር በኋላም አራት የሟቾቹ ወላጆች የልጅ ልጅ ማየት ስለሚገባቸው የዘር ፍሬዎቹን ተጠቅመው ልጅ ማግኘት ይችላሉ በማለት ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ።

ነገር ግን የማሕፀን ኪራይ ቻይና ውስጥ ሕጋዊ ባለመሆኑ ሁኔታዎች ለሟቾቹ ወላጆች ቀላል አልነበሩም። ይህን ተከትሎም የማሕፀን ኪራይ ወደምትፈቅደው ደቡብምስራቃዊ እስያ ውስጥ ወደምትገኘው ላኦስ መሄድ ነበረባቸው።

ዘር ፍሬ ከሃገር ሃገር የሚያጓጉዝ አየር መንገድ አለመኖሩ ደግሞ ለቤተሰቦቹ ሌላ ፈተና ነበር፤ ይህን ተክትሎም ፍሬውን በመኪና አጓጉዘው ማሕፀኗን ለማከራየት በወሰነችው ሴት ማሕፀን ውስጥ እንዲሆን ተደረገ።

ከዚያም በማሕፀን ኪራይ አማካይነት ልጁ ቤተሰቦቹ ከሞቱ ድፍን አራት ዓመታት በኋላ ወርሃ ታህሳስ 2017 ላይ ምድርን ሊቀላቀል ችሏል።

“ምትክ አጥተው የነበሩት አራቱም አያቶቹም ካሳ አግኝተዋል” ሲልም አንድ የቤይዢንግ ጋዜጣ ሁኔታውን ዘግቧል።

አያቶቹ ቲያንቲያን ሲሉ ሰየሙት ጨቅላ ላኦስ እንጂ ቻይና አልተወለደምና የቻይና ዜግነት ሊኖረው አይችልም የሚለው ጉዳይ ደግሞ ሌላ ራስ ምታት ሆኖ ተገኘ።

በስተመጨረሻም አራቱም የሟቾቹ ቤተሰቦች ዘረ መላቸው ተምርምሮ ከልጁ ጋር ግንኙነት እንዳለው ከተረጋገጠ በኋላ ቲያንቲያን ቻይናዊ ዜግነት እንዲኖረው ተደርጓል።

Advertisement