“ድርጅቴ ከሩስያ ጋር ጦርነት ገጥሟል” የፌስቡክ አለቃ ዙከርበርግ

                        

የፌስቡክ መሥራች እና አለቃ የሆነው ማርክ ዙከርበርግ ትላንት በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ፊት ቀርቦ ባሰማው ንግግር “ድርጅቴን በዝብዘው መረጃ ለመውሰድ ከሚፈልጉ ሩስያውያን ጋር ጦርነት ገጥሜያለሁ” ሲል ተደምጧል።

“ይህ የለየለት ጦርነት ነው። እነሱ መረጃ መበርበር ላይ እጅጉን እየበረቱ መጥተዋል” ሲል ነው ዙከርበርግ ስሞታውን ያሰማው።

ዙከርበርግ ትላንት በአሜሪካ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ፊት ሊቀርብ የተገደደበት ምክንያት “አንድ ድርጅት የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ በርብሯልና ጉዳዩን አብራራልን” ተብሎ በመጠየቁ ነው።

አልፎም ሮበርት ሙለር የተባሉቱ ሩስያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች ወይስ አልገባችም የሚለውን አጀንዳ የሚያጣሩ ግለሰብ ፌስቡክ ላይ ምርመራ እንዳከናወኑ ዙከርበርግ አሳውቋል።

በአውሮፓውያኑ 2016 መባቻ ላይ ነበር የአቶ ሙለር ቢሮ ሩስያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ሳትገባ አትቀርም የሚለውን ጉዳይ ለማጣራት ሥራውን የጀመረው።

ይህ ልዩ አጣሪ ኃይል ሩስያ በይነ-መረብን ተጠቅማ ምርጫው ላይ ጫና አሳድራ እንደሆነ የሚያጣራ ክንፍ ያለው ሲሆን ፌስቡክ ደግሞ አንዱ ምርመራ የሚካሄድበት ድር ሆኖ ተገኝቷል።

ቢሆንም ዙከርበርግ ከህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥበት ባመሸበት ምሽት ድርጅቱ መረጃ ሾልኮ እንዳይወጣ የታቸለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

ከምክር ቤቱ አባላት አንዱ የሆኑት ጆን ኬኔዲ “ፌስቡክ ቁጥጥር ይደረግበት ብዬ ማለት አልፈልግም፤ አስፈላጊ ከሆነ ግን ከማድረግ ወደኋላ አልልም። ሲቀጥል ተጠቃሚዎች ከድርጅቱ ጋር የሚያደርጉት ስምምነት ችግር አለበት” ሲሉ ሃሳባቸውን ለዙከርበርግ ነግረውታል።

በምላሹ ዙከርበርግ “የሰዎችን መረጃ ለመጠበቅ ፍፁም የሆነ ተግባር እንዳልፈፀምን እሙን ነው። ፖለቲካዊ ሃሳቦች ድርጅታችን ላይ ተፅዕኖ እንዳያመጡም ጠንክሬ አሠራለሁ” ሲል ቃል ገብቷል።

የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃ ሾልኮ ወጥቷል የሚለው ዜና በተሰማ ጊዜ ወርዶ የነበረው የድርጅቱ ድርሻ የዙከርበርግ ምላሽ ከተሰማ በኋላ በ5 በመቶ ጨምሮ ታይቷል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement