ቃርን ሊያስነሱ/ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች

                    

   ከአመጋገብ ወይም ከመጠጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰትበን ይችላል።

ምግብ አብዝቶ መመገብ፡-

በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ሰው በምንም ያህል ጊዜ ልዩነት ይሁን ወይም ምንም አይነት የምግብ አይነት ይመገብ፣ ከመጠን ያለፈ አመጋገብ/ አብዝቶ ከተመገበ ለቃር ሊዳርገው ይችላል፡፡

ስለሆነም መጥኖ መመገብ ከምግብ መጠን ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ቃር ሊከላከልልዎ ይችላል፡፡

በፍጥነት መመገብ፡-

የስነምግብ ባለሙያዎች እንደእንደሚሉት ምግብን በችኮላ/በፍጥነት መመገብ ለቃር ተጋላጭነትዎን ይጨምራል፡፡ ስለሆነም ምግብ በሚመገቡበት ወቅት በእርጋታ ቢሆን ይመረጣል፡፡

ስብነት ያላቸው ምግቦች

ስብነት የበዛባቸው ምግቦች በጨጓራችን ውስጥ ለመፈጨት ረዘም ያሉ ሰዓታትን ይወስዳሉ፡፡ ምግብ በጨጓራችን ውስጥ ለመፈጨት ረዘም ያለ ሰዓታት በወሰደ ቁጥር ደግሞ ለቃር ተጋላጭነታችንን ይጨምራል፡፡

የዚህን ተጋላጭነት ከሚጨምሩ ነገሮች ውስጥ አንዱ ደግሞ ስብነት ያላቸውን ምግቦችን አብዝቶ/ ከመጠን አሳልፎ መመገብ ነው፡፡

አሲድነት ያላቸው ምግቦች

እንደ ቲማቲም፣ ፍራፍሬዎች (ብርቱካን፣ ወይን፣ ሎሚ፣ ኮምጣጤ) ያሉ ምግቦች በራሳቸው ወይም በባዶ ሆድዎ ቢመገቧቸው ቃርን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

ፈሳሾች/መጠጦች፡-

ለቃር ሊያጋልጥዎ የሚችሉት ምግቦች ብቻ አይደሉም፤ ፈሳሾችም ቃርን በቀላሉ ሊያስነሱብዎ ይችላሉ፡፡ 

እንደ ቡና፣ ካፊን ያለበት ሻይ፣ አልኮሆልና ጋዝ ያላቸው/ካርቦኔትድ መጠጦች ለቃር ተጋላጭነትዎን ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ ቡና ጨጓራዎ ብዙ አሲድ እንዲያመነጭ ያደርጋል፤ አልኮሆል ደግሞ የታችኛው የጎሮሮ መቋጠሪያ/መዝግያ እንዲላላ በማድረግ የጨጓራ ይዘቶች ወደ ጉሮሮ እንዲመለሱ ያደርጋል፡፡

ጋዝ ያላቸው መጠጦች በውስጣቸው ካፊን ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ካፊን ባይኖራቸውም ጨጓራዎ እንዲነፋ ስለሚያደርጉ ለቃር ሊያጋልጥዎ ይችላሉ፡፡

ካፊንና ጋዝ የሌለባቸው መጠጦች ቃርን የማስከተል አቅማቸው በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ስለሆነም ካፊን የሌለው ኸርባል ሻይ፣ ወተት፣ እና ውሃ ቃርን ለመቀነስ የሚመረጡ የፈሳሽ አይነቶች ናቸው፡፡

ቾኮሌት

ቾኮሌቶች በውስጣቸው ስብና ካፊን ሊኖራቸው ስለሚችል ለቃር ችግር ሊያጋልጡዎት ይችላሉ፡፡

ቃርን ለመቀነስ የሚመከሩ

• ማስቲካ ማኘክ፡- ማስቲካ ሲጠቀሙ ምራቅ ብዙ ስለሚመርቱ ይህ አሲዱን ለማክሸፍ/ለመቀነስ ይረዳዎታል፡፡

ቀረፋ ወይም ፔፐርሜንት/ሜንት ማስቲካዎችን መጠቀም የለብንም፤ ምክንያቱም እነዚህ ማስቲካዎች የታችኛው የጉሮሮ መቋጠሪያ/መዝግያ ስለሚያላሉ ለችግሩ መባባስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡

ሌሎች ቃርን ለመቀነስ የሚረዱ ነገሮች

• እራትዎን ከመኝታ ሰዓትዎ ከ3 ሰዓታት በፊት አስቀድመው መመገብ

• ከፍ ያለ ትራስ መጠቀም

• ምግብ ከተመገቡ በኃላ ተንጋለው ያለመተኛት

• ሲጋራ የሚያጨሱ ከሆነ ማቆም

• ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል

የቃር አልፎ አልፎ መከሰት የተለመደና ብዙም ሊያሳስብዎ የሚገባ ነገር አይደለም፡፡ 

ነገር ግን ቃር በተደጋጋሚ እየመጣ/እየተከሰተ ካስቸገረዎ እንደ ጋስትሮኢሶፋጂያል ሪፍለክስ ዲዚዝ/ Gastroesophageal Reflux Disease (GERD) ያሉ ህመሞች ምልክት ሊሆን ስለሚችል የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ይጠበቅብዎታል፡፡

ምንጭ:- ኤፍ ቢ ሲ(FBC)

Advertisement