ትራምፕ፡ “በሶሪያ ጉዳይ መረር ያለ እርምጃ ያሻል”

                             

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሶሪያ ኬሚካላዊ ጥቃት ባደረሱ አካላት ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ “ቃል እገባለሁ” ሲሉ ተሰምተዋል።

“ስለ ወታደራዊ ኃይል ካወራን በርካታ አማራጮች አሉን” ሲሉ ዶናልድ ትራምፕ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። “አሜሪካ ምን ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ እንዳቀደች በቅርቡ አሳውቃለሁ” ሲሉም ጨምረው ተናግረዋል።

እንደ ትራምፕ ከሆነ በሶሪያዋ ዶማ ግዛት በተፈፀመው ኬሚካላዊ ጥቃት ላይ እነማን እንደተሳተፉ አሜሪካ መረጃው አላት።

የሕክምና ሰጭ ተቋማት በጥቃቱ ቢያንስ 12 ሰዎች እንደተገደሉ ቢናገሩም የጥቃቱ ሰለባዎች ቁጥር ከተጠቀሰው ሊልቅ እንደሚችል እየተዘገበ ይገኛል።

ሰኞ ማምሻውን በጥቃቱ ዙሪያ ከፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢማኑዌል ማክሮን ጋር የመከሩት ትራምፕ ጠንካራ ምላሽ መስጠታችን እሙን ነው ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ቴሬዛ ሜይ ጥቃቱን “ጭካኔ የተሞላበት” ሲሉ የወረፉት ሲሆን የባሽር አል አሳድ ደጋፊዎች ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

ምዕራባዊያን ሃገራት ጥቃቱን ከማውገዛቸው በፊት ተሰብስቦ የነበረው የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አሜሪካ እና ሩስያ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተውበት አምሽቷል።

የሩስያው ተወካይ ጥቃቱ የተቀነባበረ በመሆኑ የአሜሪካ ወታደራዊ ምላሽ ነገሮችን ከማባበስ ያለፈ ፋይዳ የለውም ሲሉ የአሜሪካ ተወካይ የሆኑት ኒኪ ሄሊ በበኩላቸው የአል አሳድ መንግሥትን የሚደግፉ አካላት “የሶሪያ ህፃናት ደም እጃቸው ላይ አለ” ሲሉ ወቅሳዋል።

የሶሪያ-አሜሪካ ህክምና ማህበር በደረሰው ጥቃት 500 ያክል ሰዎች እንደተጎዱ ሲያሳውቅ እስካሁን ባለው መረጃ ከ42 እስከ 60 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል።

አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ጨምሮ በርካታ ምዕራባውያን ሃገራት ጥቃቱን ከማውገዝ ባለፈ እርምጃ እንዲወሰድ ሳያሰልሱ በመወትወት ላይ ይገኛሉ።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement