የዶ/ር አብይ አህመድ የኤርትራ የሰላም ጥሪ ከኤርትራ በኩል እንዴት ይታያል?

                   

ከጥቂት ቀናት በፊት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር መንግስት ከኤርትራ መንግስት ጋር ለዓመታት የዘለቀው አለመግባባት እንዲያበቃ እንደሚፈልግ ገልፀዋል።

በዚሁም አጋጣሚ የሰላም ጥሪያቸውን ለኤርትራ መንግሥት ማቅረባቸው ይታወሳል። ይህንንም አስመልክቶ የኤርትራው ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረ-መስቀል ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ይሰጡ ከነበሩ አስተያየቶች የተለየ እንዳልሆነ ነው።

“በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ግጭት የለም የነበረውም ሙግት የተቋጨው ከ16 ዓመታት በፊት ነው። ሰላም የሚፈጠረው ኢትዮጵያ የስምምነቱን ግዴታ ስትወጣ የኤርትራን ሉዓላዊነት በማክበርና ከያዘቻቸው ግዛቶች እንደነ ባድመ ስትለቅ ነው። ለሁለቱ ህዝቦች ሰላም አስፈላጊ ነው፤ ነገር ግን ይህ ግን ዓለም አቀፉን ህግ በማክበር የተመሰረተ መሆን አለበት። ይህ ግን ከኢትዮጵያ በኩል እየተተገበረ አይደለም” ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ሰላም መፍጠር እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸውን ያስታወሱት በኢትዮጵያ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት ኤርትራዊው ዶ/ር በረከት ብርኃኔ ወልደኃብ በበኩላቸው ይህ ጥሪ የዋህነትና የኤርትራን መንግስት ባህርይን ያላገናዘበ ነው ብለዋል።

“አስመራ ላይ ያለው ስርዓት ዋናው ፀቡ ከኤርትራ ህዝብ ጋር ነው። በዓመታት ውስጥ የሚቀየር እንዳልሆነ አይተነዋል። ከአገሩ ተሰዶ እንደሚኖር አንድ ኤርትራዊ ደስ ይለኛል” ብለዋል

ምንም እንኳን ከኤርትራ ባለስልጣናት በኩል ኢትዮጵያ ከባድመ ስትወጣ ነው የሰላም ሁኔታው የሚሰምረው የሚል ቅድመ-ሁኔታ ቢያስቀምጡም ዶ/ር በረከት ችግሩ የድንበር እንዳልሆነ ይገልፃሉ።

“የኤርትራ መንግሥት ባድመን እንደ ማደራደሪያ ነው እየተጠቀመበት ያለው። የባድመ ግዛት ቢመለስም ሰላም ይፈልጋሉ የሚል ግምት የለኝም” ይላሉ።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement