የባህር ዳር እና አዲስ አበባ ታሳሪዎች እስካሁን ፍርድ ቤት አልቀረቡም

                   

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ በባሕር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማዎች ለእስር የታደረጉ ወደ ሠላሳ የሚጠጉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች እና ምሁራን እስካሁን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ወዳጆቻቸውና የቤተሰቦቻቸው አባላት ለቢቢሲ ገልፀዋል።ባለፈው ቅዳሜ በባህር ዳር የታሰሩት ከአስራ አምስት በላይ ግለሰቦች ባረፉበት ጣብያ የሚገኙ መደበኛ ፖሊሶች ምርመራ እንዳደረጉላቸው፥ ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ ግን ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንዳልቻሉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ ያሉ የታሳሪ ጓደኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።ከታሳሪዎቹ መካከል አንደኛው ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ሲሆኑ፤ የሥራ ባልደረባቸው እና በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት አቶ እንዳላማው ክንዴ፤ የዞኑ ፖሊስ ምርመራ አድርጎ እንደጨረሰ ይሁን እንጂ እስካሁን ፍርድ ቤት ሊቀርቡም ሆነ ሊለቀቁ ያለመቻላቸውን ያስረዳሉ።

የኢህአዴግ ምክር ቤት የፓርቲውን ሊቀ መንበር እንዲሁም የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ስብሰባ ላይ ተቀምጦ መሰንበቱ ታሳሪዎቹን ትኩረት እንዳስነፈጋቸው የሚገምቱት አቶ እንዳላማው ምናልባትም አሁን ስብሰባውን መጠናቀቁ፥ ሊቀ መንበርም መመረጡን ተከትሎ ሊፈቱ እንደሚችሉ ተስፋ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።ሆኖም “ቀጥሎ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይከብዳል” የሚሉት አቶ እንዳላማው ታሳሪዎቹን ዛሬ መጠየቃቸውንና የነጹህ ውሃ አቅርቦት እና የመጸዳጃ ቤት አገልግሎት ችግር እንደሆነባቸው ማስተዋላቸውንም አክለው ተናግረዋል።ታሳሪዎቹ በሥራ ላይ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚጣረስ መልኩ ያለፈቃድ ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ ለእስር እንደተዳረጉ ቢገመትም አቶ እንዳላማው እንደሚሉት ታሳሪዎቹ በትክክል ጉዳያቸው የሚመለከተው አካል ማን እንደሆነ አያውቁም።ታሳሪዎቹ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦድር ዕውቅና አግኘተው ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመሩ ወራት መቆጠራቸውን ይመሠረታል የተባለው ፓርቲ መሥራች ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።በተመመሳይ እሁድ ዕለት ‘ሕገ ወጥ’ ባንዲራን መያዝ እና ያለፈቃድ መሰብሰብ በሚሉ ምክንያቶች በአዲስ አበባ ለእስር የበቁት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች እስካሁንም ፍርድ ቤት አልቀረቡም ተብሏል።ታሪኩ ደሳለኝ ከታሳሪዎቹ መካከል አንዱ የሆነው የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወንድም ሲሆን ለቢቢሲ እንደተናገረው በታሳሪዎቹ ላይ እስካሁም ምንም ዓይነት ምርመራ ያልተከናወነ ሲሆን ጉዳያቸው በመደበኛ ፖሊስ እና በአስቸካይ ጊዜ አዋጁ አስፈፃሚ ግብረ ኃይል መካከል እየዋለለ ያለ ይመስላል ብሏል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement