ሳይጠበቅ ቻይና የገባው ባቡር ኪም ጆንግ ኡንን እንደያዘ እየተነገረ ነው

                              

በድንገት ወደ ቻይና ዋና ከተማ ቤይጂንግ ለጉብኝት ገቡ የተባሉት ከፍተኛ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣን የሃገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሳይሆኑ እንዳልቀረ እየተገመተ ነው።

ከፍተኛ የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣንን የያዘ ዲፕሎማቲክ ባቡር በጥብቅ የደህንነት ጥበቃ ስር ሆኖ ቻይና መግባቱን መጀመሪያ ላይ የዘገቡት የጃፓን መገናኛ ብዙሃን ናቸው።

ደቡብ ኮሪያ ግን የከፍተኛ ባለስልጣኑን ማንነት ለማወቅ እንዳልቻለች የገለፀች ሲሆን፤ ጉዳዩን ግን በጥንቃቄ እየተከታተለችው እንደሆነ ገልፃለች።

በባቡሩ ተሳፍረው ወደ ቻይና የገቡት ኪም ጆንግ ኡን ከሆኑ፤ ከሰባት ዓመት በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያው የውጪ ጉብኝት ይሆናል።

ስለጉዳዩ ከቻይናም ሆነ ከደቡብ ኮሪያ ይፋዊ መግለጫ እስካሁን አልተሰጠም። ነገር ግን ጉብኝቱ እንደ አንድ ከፍተኛ አርምጃ ሊታይ የሚችል ነው ተብሏል።

ባለፈው ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ያለተጠበቀ የእንገናኝ ግብዣን ከኪም ጆንግ ኡን መቀበላቸው አይዘነጋም። ይህንን እውን ለማድረግም ባለስልጣናት ከመጋረጃ ጀርባ ውስብስቡንና አስፈላጊውን የዲፕሎማቲክ ሥራ እያከናወኑ እንደሆነ ይታመናል።

ተንታኞች እንደሚሉት የሰሜን ኮሪያና የቻይና መሪዎች ሊደረግ ከታሰበው ጉባኤ በፊት ለመገናኘት ፈልገዋል። ቻይና የሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የኢኮኖሚ አጋር መሆኗ ይታወቃል።

ቶኪዮ ላይ መቀመጫውን ያደረገው ኒፖን የዜና ተቋም ባቀረበው የቪዲዮ ምስል ላይ ወደጎን ቢጫ መስመር ያለው አረንጓዴ ባቡር ታይቷል።

የቴሌቪዥን ጣቢያው እንዳለው ይህ ባቡር የኪም አባት እንዲሁም በአውሮፕላን የመብረር ፍርሃት የነበረባቸው አያታቸው ቤይጂንግን ሲጎበኙ የተጓዙበትን ባቡር ይመስላል።

በወቅቱ ኪም ጆንግ ኢል ወደ ቻይና መሄዳቸው የተረጋገጠው እዚያው ከደረሱ በኋላ ነበር።

ከቤይጂንግ ባቡር ጣቢያ ውጪ የሚገኝ የአንድ መደብር ሃላፊ ሰኞ ዕለት ከሰአት በኋላ “ያልተለመደ” ያለው እንቅስቃሴ በአካባቢው እንደነበረ ገልጿል።

“ከባቡር ጣቢያው ውጪና ፊት ለፊት ባለው መንገድ ላይ በርካታ የፖሊስ መኮንኖች ነበሩ” ሲል ነበር ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል የተናገረው።

በታይናሚን አደባባይ ይገኙ የነበሩ ቱሪስቶች አካባቢውን እንዲለቁ በፖሊሶች ሲጠየቁ እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል። ይህም ብዙ ጊዜ የሚሆነው ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሳተፉበት ስብሰባ በቅርበት ባለው አዳራሽ ውስጥ የሚካሄድ ከሆነ ነው።

በፖሊስ እጀባ የተደረገላቸው ተሽከርካሪዎች ከስብሰባው ስፍራ ወጥተው ሲሄዱ እንደታዩም የዜና ወኪሉ ዘገባ አመልክቷል።

ብሎምበርግ እንደዘገበው ደግሞ ጎብኚው ፕሬዝዳንት ኪም እንደሆኑ ገልጿል።

ነገር ግን ተንታኞች ለደቡብ ኮሪያ ዜና ተቋም እንደተናገሩት ቤይጂንግ ታዩ የተባሉት ባለስልጣን በቅርብ ተካሂዶ በነበረው የደቡብ ኮሪያው የክረምት ኦሊምፒክ ላይ የታዩት የኪም ታናሽ እህት ኪም ዮ-ጆንግ ወይም ወታደራዊው ባለስልጣን ቾኢ ሪዮንግ-ሄ ሊሆኑ ይችላሉ።

“ከሰሜን ኮሪያ ማን ወደ ቤይጂንግ እንደተጓዘ አላረጋገጥንም” ሲሉ በደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት የሚገኙ ባለስልጣን ተናግረው “ሊሆን የሚችለውን ሁሉ በማሰብ…በጥንቃቄ ሁኔታውን እየተመለከትን ነው” ብለዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement