ሩሲያ ውስጥ በደረሰ የእሳት አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 53 ደረሰ

  

በሩሲያዋ ሳይቤሪያ ግዛት የከሰል ማዕድን ማውጫ ከተማ በሆነችው ኬሜሮቮ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የገበያ ማዕከል ላይ በተነሳ እሳት 53 ሰዎች መሞታቸው ተረጋገጠ።

በእሳት አደጋው ሳቢያ ህይወታቸው ጠፍቷል ከተባሉት ሰዎች መካከል 41ዱ ህፃናት ሊሆኑ እንደሚችልኡ ሲነገር ሌሎች ከ10 የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

የገበያ ማዕከሉ ህንፃ አንደኛ ክፍልም ሊፈርስ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

እሳቱ የተነሳው በርካታዎቹ የአደጋው ሰለባዎች ሲኒማ እየተመለከቱ ባለበት የህንፃው የላይኛ ክፍል ላይ ነበር።

እሁድ ዕለት ባጋጠመው ከዚህ የእሳት አደጋ ለማምለጥ በህንፃው ውስጥ የነበሩ ሰዎች በመሰኮት ሲዘሉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ታይተዋል።

እሳቱን ለማጥፋትና የሰዎችን ህይወት ለማትረፍ 660 የሚደርሱ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ተሰማርተዋል።

በገበያ ማዕከሉ ላይ ለተነሳው እሳት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ ባለሥልጣናት ግን መንስኤውን ለማወቅ ምርመራ እያደረጉ ነው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement