ፌስቡክ ግላዊ መረጃን አሳልፎ በመስጠት ተከሰሰ

                               

የአሜሪካው ፌዴራል የንግድ ኮሚሽን ፌስቡክ የ50 ሚሊየን ተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ ለፖለቲካ አማካሪ ድርጅት አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ምርመራ እያከናወነበት ይገኛል።

የሰዎችን ግላዊ መረጃ ያለይሁንታቸው በመበርበር የተወነጀለው ፌስቡክ ከሰኞ ጀምሮ ባሉት ቀናት በገበያ ላያ ያለው ድርሻም እየወረደ እንደመጣ እየተዘገበ ነው።

የእንግሊዝና ሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ፓርላማዎች የፌስቡክ አለቃ የሆነው ማርክ ዙከርበርግ ሁኔታውን እንዲያስረዳ ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ወቀሳው ከተሰማ በኋላ በነበረው የፌስቡክ ሠራተኞች ስበሰባ ላይ ዙከርበርግ እንዳልተገኘና ስብባው በኩባንያው ምክትል ጠቅላይ አማካሪ እንደተመራ ለማወቅም ተችሏል።

በሰሜን አሜሪካ የቢቢሲ ቴክኖሎጂ ነክ ዜናዎች ዘጋቢ የሆነው ዴቭ ሊ እንደሚለው ፌስቡክና ዙከርበርግ ላይ ጫናው እጅግ በርትቷል።

ኩባንያው በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ በትራምፕ ቅስቀሳ ቡድን የተቀጠረ ‘ካምብሪጅ አናሊቲካ’ በተሰኘ ተቋም ‘መታለሉን’ ነው የፌስቡክ ቃል-አቀባይ የሆኑ ሴት ለመገናኛ ብዙሃን ያስታወቁት።

                                 

ዜናው ከተሰማ ወዲህ ቢያንስ 60 ቢሊየን ዶላር የሚሆን የገበያ ድርሻ ያጣው ኩባንያ ፌስቡክ አለቃ ዙከርበርግ ዛሬ በሚሰበሰበው የአሜሪካ ኮንግረስ ፊት በመቅረብ ስለሁኔታው ያስረዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ፌስቡክ አታሎኛል ሲል የወቀሰው ‘ካምብሪጅ አናሊቲካ’ የተሰኘ ተቋም ኃላፊ አሌክሳንደር ኒክስ በቦርድ አባላት ትዕዛዝ ከስራቸው ለግዜው መታገዳቸውም ታውቋል።

መቀመጫውን ለንደን ከተማ ያደረገው እና የአሜሪካን የምርጫ ህግጋት ተላልፏል በሚል ክስ የቀረበበት ይህ ተቋም መሰል ውንጀላዎችን አስተባብሏል።

የፌስቡክ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑ ሮብ ሼርማን የተሰኙ ግለሰብ “የሰዎችን ግላዊ መረጃ ለመጠበቅ የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም፤ እንደውም ምርመራው ይህን እንዳሳይ አጋጣሚ ይሆነናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

የወደቀ ዛፍ እንዲሉ ወቀሳ የበዛበት ፌስቡክ ለተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃ ያለው ቦታ እንዲታወቅ በሚል ከተፈበረከ ጀምሮ ያሉ የሁለት አስርት ዓመታት መረጃዎቹም እንዲጣሩ የንግድ ኮሚሽኑ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement