ቭላድሚር ፑቲን በሰፊ ልዩነት አሸነፉ

 

የሩስያው ፕሬዚደንት እንደሚያሸንፉ በተገመተው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ተፎካካሪዎቻቸውን በሰፊ ልዩነት በመርታት ለቀጣዩ ስድስት መሪ የሚያደርጋቸውን ድል ተቀዳጅተዋል።

ሩስያን በፕሬዚደንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከአውሮፓውያኑ 1999 ጀምሮ የመሩት ቭላድሚር ፑቲን ከ76 በመቶ በላይ ድምፅ በማምጣት ነው ምርጫውን ማሸነፍ የቻሉት።

ዋነኛ ተቀናቃኛቸው አሌክሲ ናቫልኚ በምርጫው እንዳይሳተፉ መታገዳቸው አይዘነጋም።

ድሉን አስመልክቶ ለደጋፊዎቻቸው ሞስኮ ላይ ንግግር ያደረጉት ፑቲን “መራጮች ያለፉትን ዓመታት ስኬቶች ከግምት ማስገባታቸው ያስደስታል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከውጤቱ በኋላ ከጋዘጤኞች “የዛሬ ስድስት ዓመት በሚደረገው ምርጫስ ይወዳደራሉ?” በሚል የቀረበላቸውን ጥያቄ ፑቲን በፈገግታ በታጀበ መልኩ “ጥያቄው ትንሽ አስቂኝ ነው። እስከ 100 ዓመቴ ድረስ እዚህ የምቆይ ይመስላችኋል? አልቆይም” ሲሉ መልሰዋል።

ፑቲን 2012 ላይ የነበረውን ምርጫ በ62 በመቶ ድምፅ ነበር ያሸነፉት። አሁን ላይ በሰፊ ውጤት ማሸነፋቸው ከመጀመሪያውም የተገመተ ነበር።

ሚሊየነሩ ኮሚኒስት ፓቬል ግሩዲኒን 12 ድምፅ በማምጣት ሁለተኛ ወጥተዋል። የፑቲን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ውጤቱን “አስደናቂ” ሲል ገልፆታል።

ምርጫው መቃረቢያ ወቅት በአንዳድ አካባቢዎች ነፃ ምግብ ሲታደል እንዲሁም በሸቀጦች ላይ ቅናሽ ዋጋ ተስተውሎ ነበር።

በድምፅ መስጫ ቦታዎች የተሰቀሉ ተንቀሳቃሽ ምስለ የሚያነሱ መሣሪያዎች አንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ አስተናባሪዎች የምርጫ ሳጥኖችን በወረቀቶች ሲሞሉ አሳይተዋል።

በምርጫው እንዳይሳተፉ የተደረጉት ዋነኛው ተቀናቃኝ ናልቫኚ ውጤቱን ሲሰሙ ጆሮዋቸውን ማመን እንዳቃታቸውና ቁጣቸውን መቆጣጠር እንደተሳናቸው ተናግረዋል።

ከምርጫው በፊት በነበረው ጊዜ ጎሎስ የተሰኘው ገለልተኛ የምርጫ ተቆጣጣሪ ቡድን በመቶ የሚቆጠሩ ፍትሃዊነት የጎደላቸው ክስተቶችን ዘግቦ ነበር።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement