ወባ፣ ታይፎይድና ታይፈስ ምንድን ናቸው?

                                               

ትኩሳትና ራስምታት በያዘኝ ቁጥር በአቅራቢያዬ ወደሚገኙ ክሊኒኮች በመሄድ እታከማለሁ፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎችም የተለያዩ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማትን ጎብኝቻለሁ፡፡ ታዲያ በአብዛኛው ‹‹ታይፎይድ እና ወባ›› ወይም ‹‹ታይፎይድና ታይፈስ›› አንዳንዴ ሶስቱም ተገኝተውብሃል እየተባልኩ መድሃኒቶች ይሰጡኛል፡፡ ለጊዜው ቢሻለኝም ሰነባብቶ ደግሞ ሌላ ራስምታት ይከተላል፡፡ አሁንም ደግሞ ግል ክሊኒክ እሄዳለሁ፡፡ ውጤቱም ተመሳሳይ ነው፡፡ በቅርቡም በተመሳሳይ ችግር ማለትም ታይፎይድና ወባዬ ተነስቶብኝ ወደ አንድ ሌላ ክሊኒክ ጎራ ብዬ ነበር ግን ሐኪሙ ‹‹ታይፎይድም፣ ወባም፣ ታይፈስም›› የለብህም፡፡ የእስከዛሬውም እነዚሁ እንደነበሩብህ እጠራጠራለሁ ብሎ ሌላ መድሃኒት ሰጠኝ፡፡ እናም ግራ ተጋባሁ፡፡ ሌሎች እንደ እኔው ግራ የተጋቡ ባልደረቦችም አሉኝ፡፡ እንዲያው የእነዚህ ሶስት በሽታዎች ወረርሽኝ ተከስቶ ይሆን? እያልን ስንነጋገር ነበር፡፡ ጉዳዩ አሳሳቢ ሆኖብናል፡፡ ለመሆኑ የበሽታዎቹ ትስስር ምንድነው? ምንና ምንስ ናቸው? እየበዙ የመምጣታቸውስ ምስጢር ምንድነው? በእርግጠኝነት በላብራቶሪ ምርመራ ሊደረስባቸውስ አይቻልምን? በየክሊኒኩስ የተለያዩ ውጤቶች እንዴት ሊከሰቱ ይችላሉ? መልሳችሁን በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡

እኔና ጓደኞቼ
በእነዚህ ኢንፌክሽኖች ዙሪያ ህብረተሰባችን የተዛባ መረጃ ያለው ይመስላል፡፡ መንስኤውም ከተለያዩ የጤና ተቋማት በተለይም ከግል ክሊኒኮች ባለፉት ጥቂት ዓመታት እየተነገረ ያለው የተዛባ መረጃ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ሰውም ተላምዶት ‹‹ታይፎይድና ወባዬ ተነስቶብኝ፣ አገርሽቶብኝ…›› እያለ ወደየክሊኒኩ የሚሄደው፡፡ በዚህ ዙሪያ ዘጋቢ ሐኪምዎም ብዙ ገጠመኞች አሉት፡፡
ለአብነት ያህል የሚከተለውን እንጥቀስ፡፡
‹‹ምን ሆነሽ ነው የመጣሽው እቱ?›› ሐኪሙ ይጠይቃል፡፡
‹‹ያቺ ወባዬ ተነስታብኝ ነው፡፡ ታይፎይድም ሳይጨምርብኝ አይቀርም፡፡ ራሴን በጣም እያመመኝ ነው››
‹‹በምን አውቀሻቸው ነው ታይፎይድ ወባ የምትዪው?›› ያክላል ሐኪሙ፡፡
‹‹አዬ ዶ/ር እኔ ሁሌ ወደየክሊኒኩ የሚያመላልሱኝ በሽታዎች መች አጣኋቸውና›› ደግሞ በሌላ ቀን ለሌላ ታካሚ ‹‹ምንህን ነው የሚያምህ ወንድሜ?››
‹‹ራሴን ነው ትኩሳትም አለኝ ዶክተር››
‹‹መቼ ጀመረህ? ሌላስ ምን ያምሃል?››
‹‹ሀገርሽ ተውብኝ ነው፡፡ በየጊዜው ይመላለስብኛል››
‹‹እነማን ናቸው?››
‹‹ታይፎይድ፣ ታይፈስና ወባ››
ሁኔታውን ለማሳየት ሁለቱን ጠቀስኩ እንጂ ተመሳሳ ገጠመኞች ብዙ ናቸው፡፡ ይህም የሚያሳየን የጤና ግንዛቤያችን ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡ አንዳንድ ለጥቅም ያደሩ ባለሙያዎችም ይህን ከማሻሻል ይልቅ ይህን ያለመግባባት ይበልጥ የሚያባብሱና ግራ የሚያጋባ መረጃ ለታካሚዎቻቸው ይሰጣሉ፡፡ እንዲህ አይነቱን ያለመግባባት እና መደናገርን ለማስወገድ ይረዳ ዘንድ ጠቅለል ያለ ማብራሪያ እነሆ፡፡
በሰውነት ላይ በሚያስከትሉት ተፅዕኖና በሚያሳዩት ምልክቶች ተመሳሳይነት በጥቅሉ ‹‹አጣዳፊ የትኩሳት በሽታዎች›› በመባል የሚታወቁ ብዙ በሽታዎች አሉ፡፡ መንስኤዎቻቸውም ቫይረስ፣ ባክቴሪያ፣ አሊያም ሌላ ተህዋሲያን ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን አብዛኞቹ የሚያሳዩዋቸው ምልክቶች ትኩሳት፣ ላብ፣ ማንቀጥቀጥ፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽ፣ ትውከትና የድካም ስሜት ወዘተ… አጠቃላይ የህመሞቹ ምልክቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም የተሟላ የላቦራቶሪ ምርመራ በሌለበት ሁኔታ አንዱን ካንዱ መለየቱ ከባድ ነው፡፡ አንዳንዴ በተሟላ ላብራቶሪም መለየት የሚከብድበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ወቅት ሐኪሞች በአካባቢው ያለው የበሽታዎቹ አንፃራዊ ስርጭት፣ የታማሚው ሁኔታ፣ ያሉት ያሉት የህክምና አማራጮች እና በሽታዎች ካልታከመ በሰውየው ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ከግንዛቤ ባስገባ መልኩ የተሻለ የሚሉትን ህክምና ይሰጣሉ፡፡
የድህነት ነፀብራቅ የሆኑት አብዛኞቹ የትኩሳት በሽታዎች ከግልና ከአካባቢ ንፅህና ጋር ከመያያዛቸውም በላይ ተላላፊም ናቸው፡፡ የታዳጊ ሀገራት ዋነኛ የጤና እክሎችም ናቸው፡፡ ቀዳሚ ዓለም አቀፍ ገዳይ በመሆናቸው የዓለም ጤና ድርጅት ቅድሚያ ከሰጣቸው በሽታዎችም አንዱ ወባ ነው፡፡
ሀገራችንም ወባ ጎጆውን ቀልሶ ከሚኖርባቸው ሀገሮች አንዷ ነች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከአካባቢያዊ አየር ብክለትና መዛባት ጋር በተያያዘ ወባ በፊት ባልተለመደባቸው አካባቢዎችም መከሰት ጀምሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳ በየክሊኒኩ በትኩሳትና በራስ ምታት የመጣን ሰው በሙሉ ‹‹ወባ፣ ከታይፎይድና ታይፈስ ተገኝቶብሃል›› እያሉ በጅምላ ማከም በራሱ ‹‹ሰው ሰራሽ ወረርሽኝ›› ፈጥሯል፡፡ ይህ ኤነቱ ‹‹አግኝተህ ምታ›› የጅምላ ህክምና መንስኤው የባለሙያዎች የብቃት ማነስ፡፡ የአቅም ማነስ፡፡ ቸልተኝነትና ትርፍ ለማግበስበስ ወይም ግራ ከመጋባትና አማራጭ ከማጣት… የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡
ውድ ጠያቂያችን በሌላም መልኩ ካየነው አንዳንድ ሐኪሞች ለወባም ለታይፎይድም የሚሆን መድሃኒት በአንድ ላይ የሚሰጡት ለበሽተኛው በማሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ ማለትም የበሽታዎቹ አይነት አንዱን ከአንዱ መለየት ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ በመሆኑ በአጋጣሚ አንዱ በሽታ ታክሞ ሌላው ሳይታከም ቢቀር በታማሚው ላይ የሚያስከትለውን አደጋ ለማስቀረት በማሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ ታካሚው ወባ ካለበት አካባቢ በመምጣቱና በሌሎችም ምክንያቶች ወባን ብቻ ቢታከምና (በላቦራቶሪ ባይገኝም እንኳን) እንደ መጥፎ አጋጣሚ የሰውየው ችግር ታይፎይድ ቢሆን ታይፎይዱ ተባብሶ የአንጀት መበሳትና መድማት ብሎም ሞት ሊያስከትልበት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ጥርጣሬ ካለና በሽተኛውን በቅርብ የመከታተሉ እድል ከሌለ ሁለቱንም ማከሙ የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡ የሐኪሙ ሁኔታዎችን ያገናዘበ ብልህ ውሳኔ ‹‹Wise clinical judgment›› የሚያስፈልገውም በእንዲህ አይነት ጉራማይሌ አጋጣሚዎች ወቅት ነው፡፡ ጠያቂያችን ታዲያ በላብራቶሪ አይለይም ወይ ብለህ መጠየቅህ አይቀርም፡፡ ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ቀጥሎ እናየዋለን፡፡
ወባ፣ ታይፎይድና ታይፈስን ለመለየት የላቦራቶሪ ምርመራዎች አስተዋፅኦ
ወባ፣ ታይፎይድ፣ ታይስ፣ ተስቦ… የመሳሰሉት አጣዳፊ የትኩሳት በሽታዎችን የሚለዩ ልዩ ልዩ የላቦራቶሪ ምርመራዎች አሉ፡፡ በተለይም ወባና ተስቦ ትኩሳቱ በተፋፋመበት ወቅት በደም ውስጥ የመገኘታቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ አንዳዴ የሚሸሸጉበት ሁኔታ ቢኖርም፡፡ በዚህ ወቅት በየስድስት ሰዓቱ ደጋግሞ ደምን መመርመር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
የታይፎይድና የታይፈስ ምርመራዎች ግን ላተረጓጎም አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡ በተለይም በሀገራችን በስፋት የምንጠቀምባቸው የምርመራ አይነቶች የዋይደል ምርመራ (Widal test) ለታይፎይድ እና ወይልፍሌክስ ምርመራ ለታይፈስ (Weilfelix test) ለታይፈስ ሲሆኑ በጥንቃቄ ካልተተረጎሙ ውዥንብርን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡
ይኸውም የላብራቶሪው ውጤት እንደ ወባ ወይም እንደ ተስቦ በቀላሉ ተህዋሱ በደም ውስጥ አለ ወይም የለም አይልም፡፡ ውጤቱ የሚለው ‹‹Weakly reactive or strongly reactive, to… antigens›› የሚል ነው፡፡
ይህም ማለት በሽታዎችን የሚያስከትሉ ተህዋሲያን በደም ውስጥ ሲራቡ የሚከሰቱ የተለያዩ ባዕድ ኬሚካሎች እንዲቦዲይ (Antigens) አሉ፡፡ ተፈጥሯዊ የመከላከል ስርዓታችን ደግሞ እነዚህን ባዕዳንን ለይቶ የሚያጠቃት ‹‹ፀረ አንቲጂን›› ኬሚካሎች ያመርታል፡፡ ‹‹Antibodies›› ይባላሉ፡፡ ታዲያ ይህን የተላት ጦር ለመከላከል እነዚህ ተከላካይ ቅመሞች በሚያደርጉት ተጋድሎ የሚፈጠረው ፍትጊያ (reaction) በደም ውስጥ በሚደረግ ምርመራ እንዲያደረጀው ሊታይ ይችላል፡፡ ይህም ከላይ በተጠቃው መልኩ ሪያክቲቭ ተብሎ ሪፖርት ይደረጋል እንደ ላቦራቶሪ ውጤት ማለት ነው፡፡
ችግሩ ታዲያ በፍትጊያው ሳቢያ የሚታየው የውህደት ውጤት (reaction) ከብዙ ጊዜ በፊት ተከስቶ በነበረና በአግባቡ ታክሞ በዳነ ወባ ወይም ታይፈስ ብሎም ሌላ ተመሳሳይ አንቲጅን ሊያመነጭ በሚችል ኢንፌክሽን አማካይነትም ሊከሰት ይችላል፡፡ ስለሆነም በደም ምርመራ ወቅት በድሮውና በአሁኑ ኢንፌክሽን ሳቢያ የሚታየው ውጤት ልዩነቱ በሪአክሽኑ መጠንና ጥንካሬ ሊሆን ይችላል፡፡ “Weakly reactive or strongly reactive, to… antigens” እየተባለ ሪፖርት የሚደረገውም ይህን ለማመልከት ነው::

ምንጭ፦ Amhara Mass Media Agency

Advertisement