በፍሎሪዳ ድልድይ ተደርምሶ ቢያንስ አራት ሰዎች ሞቱ

                                             

በአሜሪካ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ አቅራቢያ የእግረኞች ማቋረጫ ድልድይ ተደርምሶ ቢያንስ አራት ሰዎች ሲሞቱ አስሩ ደግሞ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ባለስልጣናት ተናገሩ።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሃሙስ ምሽት ተጎጂዎችን ለመታደግ ጥረት ሲያደርጉ አምሽተዋል።

862 ቶን ክብደት ያለው እና 53 ሜትር ቁመት ያለው ይህ የእግረኛ ማቋረጫ ድልድይ በአንድ ጊዜ ስምንት መኪኖችን በሚያስተናግድ መንገድ ላይ ሲደረመስ ስምንት መኪኖች ከስሩ ነበሩ።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ድልድዩ የተገነባው ባሳለፍነው ቅዳሜ ሲሆን ድልድዩን ገንብቶ ለመጨረስ የወሰደው ጊዜ ስድስት ስዓታት ብቻ ነበር።

የትራፊክ ፍሰት እንዳይስተጓጎል በሚል የድልድዩ አካላት ተገጣጥመው ነበር እንዲቆም የተደረገው።

የዓይን እማኞች እንዳሉት ድልድዩ ሲደረመስ ከስሩ የነበሩት መኪኖች የትራፊክ መብራት አስቁሟቸው ነበር።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ”ይህን አሳዛኝ ክስተት እየተከታተልኩ ነው” ብለዋል።

የፍሎሪዳ ገዢ እና የምክር ቤት አባላት አደጋው በተከሰተበት ስፍራ ተገኝተዋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Advertisement